አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ከሚሰሩ ተቋማት ጀርባ የተለያዩ አገራት ፖለቲካዊ ፍላጎት አለ

123

መስከረም 6/2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ከሚሰሩ ተቋማት ጀርባ የተለያዩ አገራት ፖለቲካዊ ፍላጎት መኖሩን ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ብሌን ማሞ ተናገሩ።

መንግስት ኃይል የመጠቀም ብቸኛው ባለቤት በመሆኑ በአሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ የአገር ሉዓላዊነትን የማስከበር ህጋዊ ኃላፊነት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

ዓለም አቀፍ የደህንነት ጉዳዮች ተመራማሪዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት መንግስት ከኃይል ርምጃ ይልቅ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት በተደጋጋሚ ሞክሯል።

ሆኖም አሸባሪው ህወሃት ለሰላም ቦታ እንደሌለውና ለውይይት እንደማይቀመጥ ከአንድም ሶስት ጊዜ ጦርነት በመክፈት በተጨባጭ አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህም በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ከመጨፍጨፉ ባሻገር የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጻረሩና የማዕከላዊ መንግስትን የኃይል የበላይነት የሚፈታተኑ የኃይል ርምጃዎች ላይ መሳተፉን ጠቅሰዋል።

ለአብነት የሽብር ቡድኑ ራሱን እንደ አንድ ሀገር መንግስት የመቁጠር፣ ራሱን የቻለ መከላከያ ሰራዊት ያለው የማስመሰልና የውጭ ግንኙነት ቢሮ ከፍቶ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር የመገናኘት ተግባራት ውስጥ መሳተፉን አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑ የጋላቢዎቹን ፍላጎት ለማሳካት አህጉራዊ ተቋማትን ከመሳደብ ጀምሮ ኢትዮጵያን የማወክ ተግባር ላይ መሰማራቱን አብራርተዋል።

የቡድኑ የ50 ዓመታት ታሪክ የኢትዮጵያን ጡት ነካሽነትና ባንዳነት እንደሚያሳይ ያነሱት ተመራማሪዋ፤ በተለይ ከምዕራባውያን ጋር የቅጥረኝነት ጉዞው አለመቋጨቱን ገልጻዋል።

ኢትዮጵያን ለማዳከም ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በመጥቀስ፤ የአሸባሪው ህወሃት ጋላቢዎች ትልቁ የሴራ መዳረሻ ኢትዮጵያን በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መክተት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ የተረጋጋና ልማት ላይ ያተኮረ መንግስት እንዲኖራት ፈጽሞ እንደማይፈልጉ በታሪክ መመዝገቡንና አሁንም መቀጠሉን በማብራራት።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦችም የመንግስትን በጎ ጥረቶች ወደ ጎን በመተው የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባራት በተዘዋዋሪ ሲደግፉ ይስተዋላል ብለዋል።

ህወሃትን ከሽብር ቡድንነት ይልቅ የአንድ ሀገር ወይም ክልል ህጋዊና ቅቡልነት ያለው አስተዳዳሪ አስመስሎ የማቅረብና ከፌደራል መንግስቱ ጋር እኩል ተወዳዳሪ የማድረግ ዝንባሌዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ከአዝማሚያዎቹ ጀርባ የብዙ ኃይሎች ሴራና ፖለቲካዊ ግብ መኖሩን በማንሳት።

መንግስት አሁን የጀመረውን የሰላም አማራጭ አጠናክሮ በመቀጠል በዲፕሎማሲው መስክ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ላይ ጫና የመፍጠር ስልታዊ ስራ ይጠብቀዋል ብለዋል።

ከሰላም አማራጩ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ፣ ህጋዊ ማዕከላዊ መንግስትነቱን የሚያረጋግጡና፣ የኃይል የበላይነቱን የሚያስመሰክሩ ርምጃዎችን መውሰዱን እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በተለይም አሸባሪው ህወሃት ተገድዶ ወደ ሰላም ጠረጴዛ እንዲመጣ ካልሆነም የጋላቢዎቹን ተልዕኮ ለማሳካት ኢትዮጵያን የማወክ ተግባሩ እንዲያከትም የማድረጉን ስራ መንግስት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም