በመጠለያ ጣቢያዎቹ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ህክምና እየተሰጠ ነው

89
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 ሰሞኑን በኦሮሚያ ልዩ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች ህክምና እየሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ። ሰሞኑን በቡራዩ፣ ከታ፣ አሸዋሜዳ፣ አንፎና ሌሎችም አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ዜጎች ህይወታቸው ሲያልፍ በርካቶችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። በአዲስ ከተማ፣ ጉለሌና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የተጠለሉ ተጎጂዎች በቂ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ በየመጠለያ ጣቢያዎቹ ጊዜያዊ ህክምና መስጫ ተቋቁሟል። ከተለያዩ አካባቢ የመጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ነዋሪዎችና መንግስት ለተጎጂዎቹ የምግብ፣ የውሃ፣ የአልባሳትና የህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ኢዜአ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ተዘዋውሮ ተመልክቷል። በተለይም ጨቅላ ህጻናት ሴቶችና አዛውንቶች በቂ ህክምና እንዲያገኙ በከተማዋ ከሚገኙ ከስድስቱም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የተወጣጡ ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ነው። በመጠለያ ጣቢያዎቹ በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ የሚኖሩበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ እንዲከሰቱ የሚያደርግ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በመሆኑም በሽታ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።  በመጠለያ ጣቢያዎቹ  እየተሰጠ ካለው ህክምና በላይ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ወደ ሆስፒታሎች ሄደው እንዲታከሙ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት የጤና ቢሮ ኃላፊው ተጎጂዎቹ ወደ መጡበት ቦታ እስኪመለሱ የህክምና አገልግሎቱ እንደማይቋረጥ አስታውቀዋል። በመድሃኔዓለም መሰናዶ ትምህርት ቤት ለተጎጂዎች ህክምና ሲሰጥ ያገኘነው የጤና መኮንን ኃይሉ ሰፈፈ እስካሁን በመጠለያ ጣቢያዎቹ የተከሰተ ተላላፊ በሽታ ባይኖርም እከክ መሳይ በሽታዎች በአንዳንድ ሰዎች ላይ መታየት መጀመሩን ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ተጎጂዎቹ ያሉበት ሁኔታ ለተላላፊ በሽታዎች መከሰት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በሌላ በኩል በዱላና በስለት ተጎድተው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ተጎጂዎች በቂ የህክምና አገልግሎት እያገኙና ጤናቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ይገልጻሉ። በግጭቱ እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ተጎጂዎቹ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ መልካም ቢሆንም በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ነገር እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም