አሸባሪው ህወሃት ‘ተቀበልኩት’ ያለው የሰላም አማራጭ ለማደናገርና ለተጨማሪ ወረራና ውድመት ጊዜ ለመግዛት መሆኑ ተጠቆመ

82

መስከረም 05 / 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን ‘ተቀበልኩት’ ያለው የሰላም አማራጭ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገርና ለተጨማሪ ወረራና ውድመት ጊዜ ለመግዛት እንደሆነ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን ገለፁ።

ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።ዋና አስተዳዳሪው ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሃት ከግጭት ውጪ የመኖር ተፈጥሮ የለውም ብለዋል።

ቡድኑ በአዲአርቃይና አካባቢው በወረራ በቆየበት ወቅት ያለምንም ርህራሄ ጭፍጨፋና ውድመት በመፈጸም ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉን ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታል፣ የውሃ ተቋም፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና መሰል መገልገያዎች የቡድኑ የጥቃት ዒላማ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በከተማዋ ያሉ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማውደሙ የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባሩ ማሳየቱን ገልፀዋል።

የሽብር ቡድኑ 100 የሚደርሱ ሴቶችን አስገድዶ መድፈሩንና በርካታ ግለሰቦችን አፍኖ ወዳልታወቀ ስፍራ መውሰዱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም አማራጭን በመከተል ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ቡድኑ በጠብአጫሪነት መቀጠሉን ጠቅሰው፤ አሁንም የሰላም አማራጩን ስለመቀበሉ ያሰራጨው መረጃ ጊዜ በመግዛት ለተጨማሪ ወረራ ዝግጅት ለማድረግ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል።

የቡድኑ አፈ ቀላጤዎች ህዝብን እንደ ህዝብ በጠላትነት በመፈረጅ ሒሳብ እናወራርዳለን በማለት የሚችሉትን ሁሉ ጥፋት እያደረሱ እንደሆነ አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንዲሉ ምንም አይነት የሰላም ፍላጎት የሌለው ቡድን መሆኑን ገልጸው፤ የሰላም አማራጭን የማደናገሪያ ስልት አድርጎ ሊጠቀምበት እንደሚችል አስገንዝበዋል።

አቅሙ በፈቀደለት መጠን ጥፋት እያደረሰ የሚገኘው አሸባሪው ህወሃት፤ ከጥፋት ድርጊቱ ለመመለስ ዝግጁ ስለመሆኑ የሚያሳይ ምልክት እንዳልታየ ተናግረዋል።

ቡድኑ የከፈተው ጦርነት በመከላከያ ሰራዊትና በሌሎች የፀጥታ ሃይሎች በገጠመው መከላከል በፈለገው ልክ ሃገርን ማፍረስና ህዝብን ማሰቃየት ባለመቻሉ የሰላም አማራጭን በተመለከተ ያነሳው ሀሳብ ማደናገሪያ እንደሆነም ገልፀዋል።

በአካባቢው በቡድኑ በደረስው ጉዳት መላ ህዝቡ መንግስትስዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በውጭ የሚኖሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እስካሁን የላቀ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም