የኢትዮጵያ ቼስ ብሄራዊ ቡድን ለኦሎምፒክ ውድድር ወደ ጆርጂያ ሊያቀና ነው

76
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 በጆርጅያ ባቱሚ በሚካሄደው 43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ  የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ይፋ ተደረገ። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን በጆርጅያ ባቱሚ በሚካሄደው የ43ኛው ቼስ ኦሎምፒያድ ጥሩ ተሳታፊና ተፎካካሪ ለመሆን አስፈላጊዉን ማጣራት አድርጎ አምስት ሴትና አምስት ወንድ ስፖርተኞችን መርጧል። በውድድሩ ላይ የሚካፈለው ልዑክ ቅዳሜ መስከረም 12 ማታ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ውድድሩ ከመስከረም 13 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚከናወንም ከወጣው መርኃ ግብር ለመረዳት ተችሏል። ከዚህ ባለፈ 43ኛውን የቼስ ኦሎምፒያድ ውድድር በዳኝነት እንዲመሩ ከተመረጡት  መካከል ኢትዮጵያዊው የፊዴ(FIDE) አልቢተር ደጀን ዘላለም ከዓለም አቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን( FIDE) ጥሪ እንደተደረገላችውና ወደ ጆርጅያ ባቱሚ እንደሚያቀኑ ታውቋል፡፡ በሴቶች ምድብ ከሚወዳዳሩ ስፖርተኞች መካከል ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አምስት ሴት ስፖርተኞች ተለይተው ታውቀዋል። ልደት አባተ በቀዳሚነት ስትመረጥ፤  ፌቨን ገብረመስቀል በሁለተኛነት የብሄራዊ ቡድኑ አባል ሆነው ተመርጠዋል። እንዲሁም ሩት ለይኩን፣ መርሃዊት ብርሃነና  አስቴር መላክ ደግሞ በማጣሪያ ውድድሩ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቃቸው የብሄራዊ ቡድኑ አባል ሆነው ተመርጠዋል። በወንዶች ደግሞ ብርሃኔ ገብረሚካኤል፣ ግሩም ተክለወልድ፣ ሐፍቶም ገብረመድህን፣ አቤል ማቲዎስና አይዳኙም ግዛቸው ተመርጠዋል። ለጆርጂያው ውድድር የተመረጡት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቅድመ ዝግጅት የሚረዳ ስልጠና ከሐምሌ 23 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ዓለም አቀፍ እውቅና በተቸራቸው ግሪካዊው የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም