ከስንቅ ዝግጅት በተጨማሪ ግንባር ድረስ ዘምተን የቀድሞ እናቶችን ድል ለመድገም ዝግጁ ነን - ሴቶች

190

ፍቼ/ነገሌ መስከረም ዐ5/2ዐ15/ኢዜአ/ ከስንቅ ዝግጅት በተጨማሪ ግንባር ድረስ ዘምተው የቀድሞ እናቶችን ድል ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የምዕራብ ጉጂ ዞን ሴቶች ገለፁ፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች አሸባሪው የህወሀት ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት በድል ለመወጣትና  የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የስንቅ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የዞኑ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ይርገዱ አያሌው ገልፀዋል፡፡

በስንቅ ዝግጅቱ ከሶስት ሚሊየን ብር የሚበልጥ የዳቦ ቆሎ፣ ቆሎና ሌሎች የደረቅ ምግብ ዝግጅቶችን ያካተቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በፊትም 165 ሺህ ብር ግምት ያለው 20 ኩንታል ደረቅ ስንቅ አዘጋጅተው  ግንባር ድረስ በመሄድ ማስረከባቸውን አስታውሰዋል፡፡  

በስንቅ ዝግጅቱ  1ዐ ሺህ የሚሆኑና በተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶች ውስጥ የታቀፉ ሴቶች ያለምንም ቀስቃሽ በራሳቸው ተነሳሽነት በየአካባቢያቸው ገንዘብ ከማዋጣት ጀምሮ በጉልበት በመሳተፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በስንቅ ዝግጅቱ ከተሳተፉት መካከል የፍቼ ከተማ ቀበሌ ዐ4 ነዋሪ ወይዘሮ ኑሪያ ኡስማን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በጉልበትና በገንዘባቸው ከሚያደርጉት በተጨማሪ በግንባር የሕወሀት ቡድንን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ እናቶች ታሪክ ጠላት ሲመጣ በጋራ መዝመት ጀግኖቹን ማበረታታትና በጦር ሜዳ የተጐዱ ወገኖችን ማከም የሴቶች ግንባር ቀደም ሚና መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጡት ወይዘሮ ፀሓይነሽ  መኮንን አሸባሪው ሕውሀት የትግራይ ታዳጊ ወጣቶችና ሕፃናት ልጆችን ለጦርነት እንዲማግድ  እድል መስጠት የለብንም ብለዋል፡፡

መንግስት የሚያቀርበውን ጥሪ ተከትለው ግንባር ድረስ በመዝመት የቀደምት እናቶችን አኩሪ የድል ታሪክ ለመድገም እንደተዘጋጁም ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፈለው አደሬ በበኩላቸው የተደራጁ ሴቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ፀጥታ ሃይል የሚያደርጉት ድጋፍ ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በምእራብ ጉጂ ዞን ሴቶች የተዘጋጀ 111 ኩንታል ስንቅ ወደ ግንባር እየተጓጓዘ እንደሆነ የዞኑ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ ያደኒ ወንድሙ ወደ ግንባር እየተጓጓዘ ያለው ስንቅ በዞኑ 9 ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደር ሴቶች ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለመከላከያ ሰራዊቱ ስንቅ ዝግጅት በዞኑ ሴቶች ብቻ አንድ ሚሊዮን 78 ሺህ ብር የሚበልጥ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ለሰራዊቱ የተዘጋጀው የዳቦ ቆሎ፣ የበሶ፣ የቆሎ፣ የጥሬ ገብስ፣ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የመኮረኒና የፓስታ ስንቅ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ወደ ግንባር በጭነት ተሽከርካሪ በመጓጓዝ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዞኑ ሴቶች የስንቅ ድጋፉን ለ5ኛ ዙር ያዘጋጁት ሲሆን "እኔም ለሀገሬ የድርሻዬን እወጣለሁ" በሚል መሪህ  የግል ፍላጎትና ተነሳሽነት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከስንቅ ዝግጅቱ በተጨማሪ የተከፈተውን ወረራ ለመመከት ሴት ወንድ ልጅ አዋቂ ሳንል ሀገር ለማዳን በጋራ እንነሳለን ሲሉም ተናግረዋል ወይዘሮ ያደኒ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም