በውሐ፣ በውሐ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

118

ባህርዳር መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በውሐ፣ በውሐ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት አልምታ የመጠቀም መብት አላት።

May be an image of 1 person and sitting

በሀገራችን 12 ተፋሰሶችና 12 እርጥበት አዘል መሬት እንዳላት በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

ከተፋሰሶቹ ውስጥ ከአዋሽና በስምጥ ሸለቆ ከሚገኙ የውሃ አካላት ውጭ ያሉት ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በአግባቡ አልምታ ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ተፅዕኖ እንዳለባት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በመጥቀስ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ይሄን መሰረታዊ ችግር ለማቃለል በሀገሪቱ ላይ የሚሰራጨውን የሃሰት መረጃ ለመመከት የሚዲያ አጠቃቀማችንን ማሻሻል አለብን ብለዋል።

ለዚህም "የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሙዩኒኬሽን" ፎረም በመመስረት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሀሰት መረጃን ለመመከት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የዚህ መድረክ ዓላማም ይሄው መሆኑን ተናግረዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በውሃ ማኔጅመንት፣ በመሬት አስተዳደር፣ በህግና ሚዲያው ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 1 person, standing and text that says 'OBN'

ከዘርፉ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቋቋም የሚያስችል የተማረ የሰው ሃይል እያፈራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በእውቀት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ጥናት በምሁራን ተዘጋጅቶ እንደዚህ ባሉ መድረኮች በማቅረብ ተቋሙ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ዶክተር ፍሬው አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሌሎች እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም