የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ቤት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ

124

 መስከረም 4 /2015  /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ቤት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ፡፡

በዛሬው እለትም የትምህርት ቤቱን የ25 ዓመታት ጉዞ የሚዘክር አውደ ርዕይ ለእይታ በቅቷል፡፡

የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ፤ አውደ ርዕዩ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችና የተማሪዎች ስራዎች ያካተተና የትምህርት ቤቱን ታሪክ፣ አሁናዊ ገጽታና  የወደፊት ዕቅዱን የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ የብሮድካስትና ኅትመትና ተግባቦት ትምህርቶች የደረሱበትን ደረጃ እንዲሁም ለጋዜጠኝነት ሙያ ያበረከተው አስተዋጽኦ ይታይበታል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ቤት በመንግስት፣ በግልና በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማፍራት ለዘርፉ ማደግ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት ተሰማርተው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የሚዎጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉንም እንዲሁ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት የተመሰረተው በ1989 ዓ.ም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጅማ በር በሚገኘው በቀድሞው የኢትዮጵያ ራዲዮ ግቢ ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት፣ በመልቲ ሚዲያ ጋዜጠኝነትና በሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ከሙኒኬሽን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጥናት በሦስተኛ ዲግሪ እያስተማረ ሲሆን ተጨማሪ የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት የስርዓተትምህርት ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም