ለከተሞች የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ የ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል---የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር

71
አዳማ መስከረም 9/2011 በተያዘው በጀት ዓመት ከ670 በሚበልጡ የሀገሪቱ ከተሞች ለሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ግንባታዎች የፌደራል መንግስት 1ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አታወቀ። በሚኒስቴሩ የፖሊሲና ፕሮግራም ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ መሐመድ ዘይኑ ለኢዜአ እንደገለፁት መንግስት ለግንባታዎቹ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከሚመድቡት በጀት በተጨማሪ የፌዴራል መንግስት የገንዘብ ድጎማውን አድርጓል ። በከተሞች ማህበራዊና አካባቢያዊ ደህንነት ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ ከሚካሄዱት ግንባታዎች መካከል የ1ሺህ 481 ኪሎ ሜትር የጥርብ ድንጋይ መንገዶችን የማንጠፍ ስራ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል ። በተጨማሪም 8 ሺህ 355 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የጠጠርና ጥርጊያ መንገዶች እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ግንባታ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀዋል ። እንዲሁም የ536 ድልድዮችና የ61 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታና ጥገና እንደሚከናወንም ተናግረዋል ። "የኤሌክትሪክና የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ከ3 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ዳር መብራቶችና፣ የውሃ መስመሮች ዝርጋታ ጨምሮ 707 የውሃ ማከፋፈያ ቦኖዎች ግንባታ ይካሄዳል" ብለዋል ። የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ቄራዎች፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያዎች፣ የህዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች፣ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎችና ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ግንባታዎችም በከተሞቹ በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች የሚካተቱ ናቸው። አቶ መሐመድ አያይዘውም በከተሞቹ በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ከሚጠበቁ 113 ሺህ ዜጎች ውሰጥ 40 በመቶዎቹ ሴቶች እንደሚሆኑ አመላክተዋል ። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ቢራሳ በበኩላቸው በከተሞች የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራዎች የአቅርቦት፣ የቅንጅት፣የጥራትና እንክብካቤ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል። "በእነዚህ ተግዳሮቶች መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ ሰነድ በዚህ ዓመት በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ በልዩ ትኩረት ይሰራል" ብለዋል ። በተመረጡ ከተሞች መሰረተ ልማቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚያመላክት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ምክረ-ሃሳብ የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ  ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚሰራጭ ሚኒስትር ዴኤታዋ  ተናግረዋል። "ሰነዱ ደረጃውን የጠበቀና የተቀናጀ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ለማመቻቸት፣የመሰረተ ልማትና አገልግሎት አቅራቢ ተቋማትን ትስስር ለማጠናከር ያስችላል" ብለዋል። የቴክኖሎጂና የክህሎት ሽግግርን በማጎልበት ልማትን የሚያፋጥን እንዲሁም የህዝብ ተጠቃሚነትና ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ የተቀናጀ ስራ ለማከናወን ሰነዱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል ። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተቀናጀ የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ መርሀ ግብር በተከናወኑ 1ሺህ 994 ፕሮጀክቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም