በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዳያስፖራ ማነቃቂያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

72
አዲስ አበባ  መስከረም 9/2011 በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዳያስፖራ ማነቃቂያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ሊያካሂድ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ። የፕሮግራሙ ዓላማ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ባሉባቸው ችግሮች ላይ በመወያየትና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማምጣት መልካም እድሎችን በመጠቀም ለአገራቸው የበኩላቸውን አስተዋዕኦ ማድረግ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል። የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መድረኩ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ ነው። በዚህም የዳያስፖራ አባላቱ አጠቃላይ መረጃ የሚያገኙበትንና ወደ አገራቸው መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውንም አፍስሰው በኢንቨስትመን መስኮች ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል። በተለይም በአብዛኞቹ ዳያስፖራዎች ጥያቄ የሚያነሱባቸውን ተቋማት በመለየት ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡና መልስ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዳያስፖራው ማህበረሰብ መረጃ የሚያገኝበትንና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በዚህም የኢንቨስትመን አካሄዶች፣ በቱሪዝም መስኮች ላይ ዳያስፖራው የሚሳተፍበትን መንገድ ለመፍጠርና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ህጎችና አሰራሮች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን አመልክተዋል። ውይይቱ የፊታችን መስከረም 19 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የሚካሄድ ነው የሚሆነው። የተለያዩ የመንግስት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአንድ ሺህ በላይ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሚገኙበት ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም