ደኢህዴን ክልሉን ቀድሞ ወደ ሚታወቅበት ሰላምና መረጋጋት እመልሳለሁ አለ

74
ሀዋሳ መስከረም 9/2011 ክልሉ ወደ ሚታወቅበት የሰላምና የልማት ቀጠና እንዲመለስ የህግ የበላይነት ማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ደኢህዴን አስታወቀ። የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በክልሉ ፀጥታና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ንቅናቄው ክልሉን መምራት ከጀመረበት ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ  በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ባልተጠበቀ መልኩ በክልሉ የተለያዩ አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶች ለዜጎች መፈናቀል ሞትና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ክልላዊ ሁኔታውን ገምግሞ ችግሩን በአስቸኳይ መፍታት የሚያስችል የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ተናግረዋል። በዚህም ክልሉ ወደ ሚታወቅበት የሰላምና የልማት ቀጠና እንዲመለስ የህግ የበላይነት ማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ ላይ ደኢህዴን ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ “የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ ቀዳሚው ተግባር ነበር” ያሉት አቶ ሞገስ በ77 መጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቃዮች የነበሩበት ጌዲኦ ዞን ከአንድ መጠለያ ካምፕ ውጭ ሁሉም ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል። በአማሮና ቡርጂ በነበረው የጸጥታ ችግር ለረዥም ጊዜ የተዘጉ መንገዶችን የመክፈትና ከህብረተሰቡ ጋር የውይይት መድረኮች እየተከናወኑ በመሆናቸው ችግሩን በተወሰነ ድረጃ መቀነስ ተችሏል፡፡ በሃዋሳ፣ በሲዳማ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች፣ በጋሞ ጎፋ፣ ዳውሮ፣የም፣ሸካ ወልቄጤና ሌሎች ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ስራው መቀጠሉን ገልጸው አሁንም ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። በዚህም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከጸጥታ ሃይሉና ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ሰላሙን የመመለስና ጥፋተኞችን በህግ የማስጠየቅ ስራው በትኩረት ይከናወናል፡፡ “በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልማት ጥያቄና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ቅራኔ መኖሩን የገለጹት አቶ ሞገስ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ክልል አቀፍ የባለሙያ ቡድን ተቋቁሞ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡ በአመራር ደረጃ ያለውን ችግር ለመፍታትም በክልሉ የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ላይ ያሉ አመራሮችን  በህዝብ በማስተቸት አመራሩን መልሶ የማደራጀት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠሩ ቀውሶች በአብዛኛው አካባቢ በአንድ ወቅት የተከሰተ በመሆኑ የህዝቡን ችግር በተገቢው መፍታት እንዲቻል በትዕግስት ሊጠብቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ “ደኢህዴን የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅና የሚታወቅበትን ህብረ-ብሄራዊነት ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ የተነሳበት ወቅት ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡ በክልሉና ከክልሉ ውጭ በዜጎች ላይ ለደረሰው ሞትና መፈናቀልም ድርጅቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው የድጋፍና ወንጀለኞችን የማስጠየቁን ስራ ደኢህዴን በቅንጀት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም