አገር ውስጥ የተገጣጠሙ ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለአርሶና አርብቶ አደሮች ተላለፉ

134

መስከረም 3/2014/ኢዜአ/ የኦሮሚያ ክልል በ600 ሚሊዬን ብር ወጪ አገር ውስጥ የተገጣጠሙ ከ 16 ሺህ በላይ ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች አስተላለፈ።


ክልሉ ለግብርናው ዘርፍ እድገት ልዩ ትኩረት ስጥቶ በመስራት ውጤት እያገኘበት መሆኑ ተገልፇል።

በዚሁ መርሓ ግብር ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እስካሁን በግብርና ዘርፍ በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከ80 በመቶ በላይ ትኩረቱን ለግብርና ዘርፍ እድገት ሰጥቶ ጠንካራ ስራ እያከናወነ  መሆኑን  ነው የገለጹት።

የክልሉ መንግስት ቀዳሚና ዋናው ስራ ግብርና መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽመልስ የክልሉ አመራር፣ በጀትና አጠቃላይ ትኩረት ለግብርና የተሰጠ መሆኑንም አክለዋል።

''ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው የሕዝባችንን ምኞትና ፍላጎት ማሳካትና የሕዝቡን ኑሮ መለወጥ የምንችለው'' ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

በመስኖ ልማት ዘርፍ የውኃ ማቆር ስራ፣ የተለያዩ ግድቦችን መስራት በተለይም በቆላማ አካባቢዎች፣ በስፋት የውሃ ፓምፕ የማቅረብ ስራ በዋናነት እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

በውሃ ፓምፕ ስርጭት ብቻ ባለፉት ሶስት ዓመታት 38 ሺህ ፓምፕ የተሰራጨ ሲሆን በዚህም የተሻለ ለውጥ እየተገኘ ነው ብለዋል።

በዚህ ስራ ውስጥ የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው 'ጀብዱ ሞተርስ' ውጤታማ ስራ እያከነወነ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባልም ነው ያሉት።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ መንግስት የልማት ድርጅቶች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ 'ጀብዱ ሞተርስ' ውጤታማ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን መስክረዋል።

በዚህ ስራውም በዛሬው እለት ለአርሶ አደርና ለአርብቶ አደር የሚተላለፉ ከ 16 ሺህ በላይ የውሃ ፓምፖች መገጣጠም መቻሉን ነው የተናገሩት።

ይህም የውሃ ፓምፖችን ከውጪ ለመግዛት የሚወጣውን ወጪ ከማስቀረት ባሻገር በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የሚደረግ ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ለግብርና ዘርፍ ሜካናይዜሽን ልዩ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውሰዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት ግብርናውን ማዘመን የሚችሉ 500 አይነት የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑን ተናግረዋል።

ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ15 አይነት የማይበልጡ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች እየገቡ መሆኑን ተናግረው በዚህም የኦሮሚያ ክልል የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም