በአፍሪካ በህጻናትና ወጣቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ ተባለ

48
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 በአፍሪካ በህጻናትና ወጣቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ውጤታማና መረጃን መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎችና መርኃ ግብሮች ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ። ህጻናትና ወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ አፍሪካ አገራት ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ በልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መቋጫ እንዲያገኙ ግብ ተቀምጧል። ይህን ተከትሎም የአፍሪካ አገራት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ቢሆንም ጥናትን መሰረት አድርጎ መከላከል ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ነው የተገለጸው። የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል። መርሃ ግብሩ ስለ ልጆች ጥቃት ምን እናውቃለን? እና በተሻለ ለመከላከል ምን ማድረግ እንችላለን? በሚሉ መሪ ጥያቄዎች ነው የተካሄደው። ቤኒን፣ ኮትዲቯር ፣ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቶጎ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል። የ"አፍሪካን ፓርትነር ሺፕ ቱ ኢንድ ቫዮለንስ አጌይንስት ችልድረን" አስተባባሪ ሚስ ዶሪስ ሩስ እንዳሉት በአፍሪካ በልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እንቅስቃሴ ቢኖርም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አልተገኘም። ለዚህም አገራቱ ወጥ በሆነና በተደራጀ መንገድ የህጻናት ፖሊስን አለመተግበራቸውና ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ አለመወሰዱ ከምክንያቶቹ መካከል እንደሚካተቱ ይገልጻሉ። ጥቃቱን ለመከካከልም ጠንካራ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አስተባባሪዋ ፖሊሲ አውጪዎች በአንድ አገር ውስጥ ምን አይነት ጥቃቶች ይፈጸማሉ? ምንያህል ድግግሞሽ አለው የሚሉ መረጃዎችን መሰረት አድርገው ፖሊሲ መቅረጽ እንዳለባቸው ተናግረዋል። የአፍሪካ አገራትም በመስኩ በቂ ሀብት በመመደብ፣ በሙሉ ትኩረትና ቁርጠኝነት መስራት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል። በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የህጻናት ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ ካሪን ሀስለር በበኩላቸው በአህጉሪቱ ጥቃትን የመከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም