የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር ፈቺ በይነ መረብ በማበልጸግ ዓለም አቀፍ እውቅናን እያተረፉ ነው -ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና

174

ጷጉሜን 5/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር ፈቺ በይነ መረብ በማበልጸግ ሀገርአቀፍና ዓለምአቀፍ እውቅናን እያተረፉ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአፍሪካ ሲልከን ቫሊ በተሰኘ ኩባንያ ትብብር የተዘጋጀ ቴክኖሎጂን የማበልጸግ ውድድር በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ተካሂዷል።

በውድድሩ ታካሚዎች የህክምና ታሪካቸውን በቀላሉ በስልካቸውና ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ማግኘት የሚያስችሉ፣ በኦንላይን የላይብረሪ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የተሻለ ምግብን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልባቸውና  ሌሎች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንዳሉት፤ ተማሪዎች የሕይወት ዘመን ክህሎት አግኝተው ሀገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ተቋማትን እንዲቀላቀሉ  ዩኒቨርሲቲው ጥረት እያደረገ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአፍሪካ ሲልከን ቫሊ ጋር በቴክኖሎጂ ዘርፍ  ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች አወዳድሮ  በዓለምአቀፍ ትላልቅ ኩባንያዎች ስልጠና እንዲያገኙ  አድርጓል።

ለውድድር ከቀረቡት 75 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች  እንደ ጉግልና ሌሎች ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመቀጠር ዕድልንም አግኝተዋል።

በሀገር ውስጥም ችግር ፈቺ በይነ መረብ በማበልጸግ የኢንዱስትሪ ፍላጎት የሚያሟሉና የህብረተሰቡን መረጃን በቀላሉ የማግኘት ችግርን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የገበያውን የኢንዱስትሪ ፍላጎት የሚያሟሉና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ  ቴክኖሎጂዎችን እንዲያመርቱ ድጋፍ ያደርጋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን እየሰራ ነው ብለዋል።

ሀገር አቀፍ ኩባንያዎች ከአፍሪካ ሲልከን ቫሊ ተሞክሮውን በመውስድ ተማሪዎችን በማሰልጠን ገበያውን እንዲቀላቀሉም ፕሮፌሰር ጣሰው ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሲልከን ቫሊ ኩባንያ  የኢትዮጵያ ተጠሪ ኢንጅነር ውብአየሁ ማሞ በበኩላቸው ችግር ፈቺ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ ተማሪዎችን ለገበያው ብቁ እያደረግን ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ እውቀቶች ያሏቸው ምሩቃን እድሉን ባለማግኘት ብቻ ዓለምአቀፍ ገበያውን  መቀላቀል አለመቻላቸውን አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት በተጀመረው የሙከራ ስራ ከተፈተኑ 50 ተማሪዎች  25 በመቶ የሚሆኑት በጎግል ኩባንያ የመቀጠር እድል አግኝተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም ችለዋል ነው ያሉት።

ዘንድሮ 120 ተማሪዎች ስልጠና ያገኙ ሲሆን 90 የሚሆኑት በዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ለማስፈተን ዝግጅት መጠናቀቁን በማንሳት።

ስልጠናውን እያገኙ ያሉ ተማሪዎች በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የህይወት ከህሎት ስልጠና አግኝተው ገበያውን እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌሎች ተማሪዎችም ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችና ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ከሀገር አልፎ ዓለምአቀፍ ገበያውን መቀላቀል እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።  

የበለጸጉ በይነ መረቦች ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ ሁሉም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በተደረገው ውድድር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ በይነ መረብ  ያበለጸጉ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች  ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም