ከስድስት ሺህ በላይ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች መደበኛ ንግድን ተቀላቀሉ

59
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 መደበኛ ባልሆነ የጎዳና ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ከስድስት ሺህ በላይ ነጋዴዎች ወደ መደበኛ ንግድ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ። ቢሮው ወደ መደበኛ ንግድ ያልገቡ የጎዳና ነጋዴዎችን ህጋዊ ለማድረግ የመስሪያ ቦታ ማዘጋጀቱንም አስታውቋል። የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንግድ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መስፍን አሰፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ንግድ ቢሮው ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ባደረገው ምዝገባ 24 ሺህ 778 መደበኛ ያልሆኑ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከዚህም 16 ሺህዎቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከክልል የመጡ ናቸው። እነዚህ ነጋዴዎች በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የፀጥታ ችግር፣ ህገ-ወጥ ንግድ መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። ቢሮው እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል ነጋዴዎቹን ህጋዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንና እስካሁን 6 ሺህ 502 ነጋዴዎችን በመመዝገብና የንግድ መለያ ቁጥር በመስጠት ወደ መደበኛ ንግድ ማስገባቱን ገልጸዋል። ቀሪዎቹም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓም ድረስ የነዋሪነት መታወቂያ እና የስራ አጥነት ማስረጃ በመያዝ በየወረዳቸው በመመዝገብ ህጋዊ ነጋዴ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ቅድሚያ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚሰጥ ቢሆንም ከክልሎች ለመጡ ነጋዴዎችም ምዝገባና የስራ ቦታ እደላ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች በተዘጋጀላቸው ቀንና ሰዓት እንዲሰሩ ለማድረግ 185 ቦታዎች ተመርጠው 129ኙ ፀድቀው ለስራ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በ129ኙ ቦታዎችም ለ11 ሺህ 193 ነጋዴዎች የሚሆኑ የንግድ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። ህጋዊ የሆኑት 6 ሺህ 502ቹ በነዚህ ቦታዎች ስራ የጀመሩ ሲሆን የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም በአልባሳትና ጫማ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል። ወደ መደበኛ ንግድ መግባታቸው ተመዝግበው ግብር ለመክፈል እና ህገ-ወጥነትን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል። በተባለው ጊዜ ያልተመዘገቡ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ መስፍን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም