ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋን ወደ ቀደሞ የንግድ ማዕከልነቷ እየመለሳት ነው-- ከንቲባ ከድር ጁሀር

202

ድሬዳዋ ፤ ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በመቋቋማ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ በመምጣት ድሬዳዋን ወደ ቀደሞ የንግድ ማዕከልነቷ እየመለሳት ነው ሲሉ ከንቲባ ከድር ጁሀር ተናገሩ።

በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር በ200 ሚሊየን ብር የተገነባ  "ዜማ"  የቀለም ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ  የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር እንደገለጹት ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የቀለም ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ለበርካታ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።

ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ጋር ተያይዞ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ድሬዳዋን ወደ ቀደሞ የንግድ ማዕከልነቷ እየመለሳት ነው ብለዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ።

የዜማ ቀለም ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀይለየሱስ ሰለሞን በበኩላቸው ፋብሪካው በ200 ሚሊየን ብር መገንባቱን ገልጸዋል።

ፋብሪካው በግንባታ ዘርፍ የሚታየውን የቀለም እጥረትና ጥራት ክፍተት ለማስተካከል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማንሳት  በቀን 5 ሺህ ሊትር ቀለም እንደሚያመርትና ለ150 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ለጎረቤት ሀገራት ምርቱን እንደሚያቀብ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ፋብሪካ ኳርትዝ፣ የዝገት መከላከያ፣ ዜማ ሱፐር ፕላስቲክና የግድግዳ ቀለሞች እንደሚያመርት አስረድተዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ከንቲባውን  ጨምሮ ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም