የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አህጉራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የሰው ኃይል ለማልማት የልህቀት ማዕከላት በማቋቋም እየሰራ ነው

46
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አህጉራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የሰው ኃይል ለማልማት የልህቀት ማዕከላት በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ። አዳዲስ የልህቀት ማዕከላትን በማቋቋም የሰው ሀይል ልማት ላይ እንደሚሰራ ያስታወቀው ዩኒቨርሲቲው በአለም ባንክ ድጋፍ ባቋቋማቸው ማዕከላት ከሚያስተምራቸው የሁለተኛ ዲግሪ 100 እና የሶስተኛ ዲግሪ 30 ተማሪዎች ውስጥ 20 በመቶዎቹ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው የመጡ ናቸው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከላት በማቋቋም ከሌሎች መሰል ተቋማትና አገሮች ጋር በመተባበር ለመስራት አቅዷል። ዩኒቨርሲቲው ያለውን የሰው ኃይል አቅም በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት በአዳዲስ የትምህርት መስኮች ሰፊ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በመምህራን ልማት፣ ከጦርነት በኋላ መልሶ በማገገም፣ በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በኤሌክትሪሲቲና ኃይል ዘርፍ የልህቀት ማዕከላት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑንም ነው የገለፁት። እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ገለፃ፤ የልህቀት ማዕከላቱን ለማቋቋም የስዊድን መንግስት፣ የአፍሪካ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ማህበርና ትምህርት ሚኒስቴር ወጪውን እየደገፉ ነው።  ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ባቋቋማቸው የልህቀት ማዕከላት የተለያዩ ትምህርት መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተው ለሀገር ውስጥና የውጭ ተማሪዎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት በተጨማሪ ከ150 በላይ የአጫጭር ጊዜ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል። በልህቀት ማዕከላቱ ውስጥ ትምህርት መሰጠት ከጀመረበት ካለፈው አመት ጀምሮ ከ60 በላይ የሚሆኑ ወረቀቶች ተዘጋጅተው ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ጆርናሎች ላይ መታተማቸውን ፕሮፌሰር ጣሰው ገልጸዋል። የልህቀት ማዕከላቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ራሳቸውን ወደ ማስተዳደር እንዲሸጋገሩ የሚሰጡ የትምህርት መርሃ-ግብሮችን በማስተዋወቅ ተማሪዎች ከፍለው እንዲማሩ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዩኒቨርሲቲዎች ከአንድ እስከ ሶስት የልህቀት ማዕከላት እንዲያቋቁሙ እንደሚደረግ ታቅዷል። እቅዱን ማሳካት ለትምህርት ጥራትና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤታማነት ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራ የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም