በዛሬው እለት ፈቃድ የተሰጠው ሰላማዊ ሰልፍ የለም- ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

101
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ለከተማ አስተዳደር ጥያቄ ያለመቅረቡን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት የተለያዩ "በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄዳል" የሚሉ መረጃዎች ቢናፈሱም ለከተማው አስተዳደር የቀረበ ጥያቄ የለም። "መረጃው ከወሬ ባለፈ እስካሁን ህጋዊ ፈቃድ አልተጠየቀም፤ እስካሁንም በከተማዋ የሰልፍ እንቅስቃሴም የለም" ብለዋል። ህብረተሰቡ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያካሂድ ሲፈልግ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ጥያቄ ማቅረብና ፈቃድ ማግኘት እንደሚጠበቅበት የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ግን የህብረተሰቡን እንቅስቃሴና ሰላም የሚያውክ መሆኑን ተናግረዋል። የዚህ ዓይነቱ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖር የሚደረግ እንቅሰቃሴ ካለ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በመጠቆም ሊያስቆም እንደሚገባ ገልፀዋል። በተያያዘ ዜናም "አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰሞኑን ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ወጣቶች በፖሊስ እየታፈሱ ነው የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው "ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እስካሁን "ፖሊስ በጅምላ ያፈሰው ወጣት የለም" ብለዋል። በህብረተሰቡ ጥቆማና ባለው መረጃ መሰረት በቡራዩና በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ለነበረው አለመረጋጋት ተሳትፎ የነበራቸው ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ተግባር እንደቀጠለ ጠቁመው፤ ግጭቱ በነበረባቸው አካባቢዎች ወደቀደመው ሰላም እየተመለሱ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም