ፍኖተ ካርታው ሀገራዊ ለውጦችን ማገናዘብ አለበት---የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ባለድርሻ አካላት

64
አሶሳ መስከረም 9/2011 አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በቀጣይ በሀገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጦችን ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ባለድርሻ አካላት ገለጹ። በአሶሳ ከተማ በፍኖተ ካርታው ዙሪያ እየተካሔደ ባለው ውይይት ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ አበበ ጎሹ እንዳሉት በክልሉ የተከናወነው የመንደር ማሰባሰብ ትምህርትን ጨምሮ የተጀመሩ የትምህርት ተቋማት በሚገባ ተግባራዊ ባለመሆናቸው ነዋሪዎች ወደ ቀድሞው አካባቢ እየተመለሱ ነው፡፡ የትምህርት መሠረተ ልማቶች ወደ ፍኖተ ካርታው አፈጻጸም ሲገባ እንቅፋት ሊሆኑ ስለሚችሉ ከወዲሁ ትኩረት እንደሚያሻቸው ተናግረዋል። አቶ ጆንሰን ዱጋስ የተባሉ ተሳታፊ ደግሞ እየወረደ የመጣው የመምህራን እና የተማሪዎች ስነ-ምግባር ማሻሻል ለትምህርት ጥራት ቁልፍ በመሆናቸው በፍኖተ ካርታው ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ሀገራዊ ስሜትን እና የሠላምን ታላቅነት የሚያሰርጹ የትምህርት ፕሮግራሞች በመደበኛነት እንዲካተቱ ማድረግ በፍኖተ ካርታው ሊሰመሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል። “አሁን በውስን ቋንቋዎችና በመጀመሪያ ደረጃ ብቻ የሚሰጠው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ተጠናክሮ በሁሉም ቋንቋዎች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል፡፡ አቶ ሰውነት ውብሸት የተባሉ ተሳታፊ ደግሞ ፍኖተ ካርታው ሀገሪቱ በቀጣይ 15 ዓመታት የምትከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና ከግምት እንዲያስገባ ጠይቀው ከክልላዊ ይልቅ ሀገራዊ እይታ ያለው በመሆኑ በአፈጻጸም ወቅት ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል። በየጊዜው እየናረ የመጣው የግለሰብንም ሆነ የመንግስትን ኢኮኖሚያዊ አቅም እየተፈታተነ የሚገኘውን የትምህርት ወጪ ፍኖተ ካርታው ማገናዘብት ያለበት ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል። አክለውም በፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተቀመጡት አቅጣጫዎች ከዚህ ቀደም እንደገጠመን ሙሉ በሙሉ ባይሳኩ ሌሎች አማራጮች ሊካተት እንደሚገባም ተናግረዋል። የክልሉ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ አበራ “ፍኖተ ካርታው ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ለውይይት መቅረቡ ለትምህርት ጥራት መሻሻል አዲስ አካሄድ መከተል መጀመራችን ያሳያል” ብለዋል፡፡ “አዎንታዊ አድልዎ ታዳጊ ክልሎችን ለማብቃት የሚረዳ ቢሆንም በፍኖተ ካርታው በተለይም ትውልድን የሚቀርጹ መምህራን የማዘጋጀት ጉዳይ ከኮታ ይልቅ ብቃትን ማዕከል ቢያደርግ” ሲሉ አብራርተዋል። “ባለፉት ዓመታት በትምህርት አስተዳደር ዘርፍ ያልፈጸምናቸውን ችግሮችን ከፍኖተ ካርታው ጋር በማገናኘት ብዥታ ውስጥ ልንገባ አይገባም” ብለዋል፡፡ በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ-ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ሸምሰዲን መሃመድ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ወደ ትግበራ የገባ ሳይሆን በረቂቅ ደረጃ የሚገኝ ሰነድ እንደሆነ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ ህብረተሰቡን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቀጣይ እንደሚወያዩበት ገልጸው በውይይት የተገኙ ማዳበሪያ ሀሳቦች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ፍኖተ ካርታው ሲጸድቅ የሚተገበር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በአሶሳ ከተማ እየተካሔደ ያለው ውይይት በክልሉ የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ሲሆን ለፍኖተ ካርታው ማዳበሪያ ሃሳቦችን በመስጠት ዛሬ እንደሚጠበቅ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም