የሀገር ሽማግሌዎቹ ሊደርስ የነበረውን ጉዳት በባህላዊ ስርዓት ታደጉ

63
አርባ ምንጭ መስከረም 9/2011 በአርባምንጭ ከተማ በተጠራው ሰልፍ ጉዳት እንዳይደርስ የሀገር ሽማግሌዎች የተጠቀሙት ባህላዊ ስርዓት የሚደነቅ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የአርባምንጭ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ የትናየት ተክሉ እንደተናገሩት፤ የሀገር ሽማግሌዎቹ እርጥብ ሳር በመያዝ የወጣቶችን ቁጣ በማብረዳቸው ባንኩ ከአደጋ ተርፏል። ባንኩ ላይ ዘረፋና ቃጠሎ እንደደረሰ በአንዳንድ ሚዲያ የተገለጸው ዘገባ ሐሰት መሆኑን ገልጸው፤ ከሽማግሌዎቹ እርቅ አስቀድሞ በተወረወረ ድንጋይ መስተዋት መሰንጠቅና ታፔላው ላይ ከደረሰ አነስተኛ ጉዳት በስተቀር የከፋ ችግር እንዳልደረሰ ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ በባህላዊ ስርዓት ተጠቅመው ባይከላከሉ ኖሮ በወጣቶቹ ቁጣ ባንኩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደነበረ ጠቁመው ችግሩን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። የባንኩ የጥበቃ ሰራተኛ አቶ ዘላለም ካሌብ በበኩላቸው "የሀገር ሽማግለዎቹ የተቆጡ ወጣቶችን የመለሱበት ስርዓት የሚደነቅና አስተማሪ ነው ሲሉ" ገልጸዋል። ችግሮችን ከስሜትና ከሃይል ይልቅ በተረጋጋ መንፈስ ተወያይቶ መፍታትን ከሃገር ሽማግሌዎች መማር እንደሚቻል ተናግረዋል። በወቅቱ ወጣቶችን ወደተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ ኃላፊነታቸውን ከተወጡ የሃገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆኑት አስር አለቃ አገና አበራ እንደገለጹት በጋሞ ባህል የራስ ባልሆነ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ "ጎሜ" ይባላል። ተንበርክኮ ሳር መያዝ ለንብረት ብቻ ሳይሆን ጋሞ የራስ ያልሆነውን ሁሉ የሚከላከልበትና የሚያከብርበት ባህል መሆኑንም ገልጸው በብሔረሰቡ ባህል ወጣቶችን ጨምሮ ለስርዓቱ የማይገዛ እንደሚጠየቅ ተናግረዋል። ይህንን ስርዓት ተጠቅመው ወጣቶቹን ከስሜታዊነት ማብረድ በመቻላቸው በሁከትና ግርግሩ ምክንያት ሊወድም የነበረ ንብረት ማትረፋቸውንና በሰው ላይም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መታደጋውን ጠቅሰዋል፡፡ ሌላው ከሽማግሌዎች ጋር ከአባቶች ጋር እርጥብ ሳር ይዘው የተንበረከኩት አቶ አፈወርቅ ዘውዴ በድንገት የተፈጠረው ችግር ለመከላከል እንደ ብሔረሰቡ ባህል በስህተት የሚጓዙ ወጣቶችን መከላከል ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ሌሎች ወጣቶች ለስርዓቱ ተገዥ በመሆናቸው ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በማስቀረት አካባቢውን ማረጋጋት መቻሉን አስረድተው ለወደፊትም ይህን ባህል ይበልጥ ለማሳደግና ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ቡራዩ ከተማና አካባቢው ከቀናት በፊት የደረሰውን ግጭት ተከትሎ ከትላንት በስቲያ በአርባምንጭ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በተፈጠረው ሁከት መቋረጡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም