ከነገ ጀምሮ ለ30 ቀናት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

108

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) ከነገ ጀምሮ ለ30 ቀናት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የመንገድ ላይ የትራፊክ ቁጥጥር እና ግንዛቤ የማስጨበጫ ንቅናቄ እንደሚካሄድ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ገልጿል፡፡

”አደጋውን ለመቀነስ እኔም ድርሻ አለኝ!” ከጳጉሜን እስከ ጳጉሜን እንደርሳለን! በሚል መሪ ቃል ነው ንቅናቄው የሚካሄደው።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ በሰጡት መግለጫ በሀገሪቱ በሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ከነገ ጀምሮ እስከ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም የጳጉሜ ወር ልዩ የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ንቅናቄና የቁጥጥር መርሃ ግብር መዘጋጁቱን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም በጳጉሜን አምስቱን ቀናት የተለያዩ መርሃ ግብሮች በማውጣት የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

በነገው ዕለት በሀገሪቱ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ባለባቸው አካባቢዎች የመንገድ ላይ የትራፊክ ቁጥጥርና ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

በዚህም ቀላል የትራፊክ ህግ ጥሰት ለፈጸሙ አሽከርካሪዎች የማስተማርና ምክር የመስጠት ተግባር እንደሚከናወን በማንሳት።

በተመሳሳይ ከጳጉሜ ሁለት እስከ ጳጉሜ አምስት ሰዎችን የትራፊክ አደጋን መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ውይይት እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

በትራፊክ አደጋ ምክንያት የደም እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች ደም የመለገስ ፣ ለትራፊክ አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች ድጋፍ የማድረግ እና ለአቤት ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የፌደራል ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥርና አደጋ ምርመራ መምሪያ የስልጠናና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ይስሃቅ ቱኬ በበኩላቸው "የትራፊክ አደጋ የነገ ሀገር  ተረካቢ የሆኑ አምራች ሃይሎች እያሳጣን ነው" ብለዋል፡፡

አደጋውን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግን በተገቢው መልኩ ሊተገብሩ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነቱ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም