ህወሐትና ደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤዎቻቸውን ሊያካሒዱ ነው

219
ሀዋሳ መስከረም 8/2011 የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ /ህወሓት/ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን በመቀሌና ሃዋሳ ድርጅታዊ ጉባኤዎቻቸውን ሊያካሒዱ ነው። የህወሐት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አለም ገብረዋህድ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ከመስከረም 16/2011 ጀምሮ በሚካሔደው 13ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች እንዲሳተፉ ግብዣ ቀርቧል። በድርጅታዊ ጉባኤው 1ሺህ 300 በድምጽ ሰጪነት እና 350 በታዛቢነት በድምሩ 1ሺህ 650  ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ገልጸው ጉባኤው ለቀጣይ 10 አመታት የሚያገለግሉ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችንና አፈፃፀማቸውም እንደሚገመግም የተናገሩት ኃላፊው የማእከላዊ ኮሚቴ ምርጫ እንደሚካሔድና ህዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው ወጣት ምሁራንና ሴቶችን በብዛት ለማካታት መታቀዱን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዜና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ከመስከረም 18 እስከ 21 /2011 ጀምሮ ድርጅታዊ ጉባኤውን እንደሚያካሔድ አስታውቋል። የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደገለጹት "የህዝቦች አንድነት ለሁለንተናዊ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይሄው ጉባኤ የክልሉን ህዝቦች አንድነት የሚጠያናክርና እመርታዊ ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን  ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። የደኢህዴንን የተሟላ የለውጥ ሂደት ማጠናከር የሚያስችሉ ስድስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ጥናት ተካሂዷል ያሉት ሃላፊው እያደገ ለመጣው የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ እንደሚሆንም  ተናግረዋል፡፡ “የክልሉን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ጠብቆ ማቆየት እንዲቻል ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚቱ በጥናቱ የተካተቱ ሲሆን ችግሮቹን ለመለየት የሚረዳና የምሁራን አስተያየትም የተካተተበት መረጃ የሚቀርብበት ጉባኤ መሆኑ ለየት ያደርገዋል” ብለዋል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ተመስርቶ በሚካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤው በ9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች የተፈጸሙበት ሂደትም ይገመገማል ያሉት ኃላፊው፤ በሃገር ደረጃ ለመጡ ለውጦች የደኢህዴን አስተዋጽኦና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ይወያያል፡፡ ከ1ሺ ስምንት መቶ በላይ የጉባኤው ተሳታፊዎች በተጨማሪ ታዋቂ ግለሰቦችንና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉም ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም