ኮሚሽኑ በቡራዩ የደረሰውን የመብት ጥሰት አጣርቶ ለህዘብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ

81
አዲስ አበባ  መስከረም 8/2011 ከቡራዩና  አካበባቢዋ የተፈናቀሉ ዜጎች ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ከቡራዩና አካባቢው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል። ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው እንዳሉት፤ በህገ መንግስቱ የሰፈሩት የዜጎች ሰብዓዊና ህገ_መንግስታዊ መብቶቻቸው ተጥሶ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ''ይህም የዜጎችን  ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ያሳጣ መሆኑን ኮሚሽኑ ተገንዝቧል'' ብለዋል። ስለሆነም በዜጎች ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማጣራት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደረግ የገለጹት ዶክተር አዲሱ በህገወጦች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም እንደሚሰራ ተናግረዋል። ''በምልከታው ችግሩ ኮሚሽኑ ካሰበው በላይ ጉዳት መድረሱን ተመልክቷል'' ያሉት ዶክተር አዲሱ ዜጎች የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነታቸውን ያጡበት ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ችግሩ በተፈጠረበት አጋጣሚ መንግስት ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጉ የሰብዓዊ መብት መጣሱን የገለጹት ኮሚሽነሩ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ተናግረዋል።  ዜጎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ወደ አዲስ አበባ መጠለያ ከመጡ በኋላ የአዲስ አበባ ህዝብና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እያደረጉላቸው ያለው ድጋፍ የሚያስደስት እንደሆነ መታዘባቸውንም ገልጸዋል። ነገር ግን በአካባቢው ነዋሪ ብቻ ችግሩ የሚቃለል ባለመሆኑ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል።  በመሆኑን ተፈናቃዮች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት በአስቸኳይ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አሷስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም