ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዳግም ጦርነት የቀሰቀሱ የአሸባሪው ሕወሃት ኅይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመለሱ ጫና እንዲያደርግ ተጠየቀ

149

ነሐሴ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዳግም ጦርነት የቀሰቀሱ የአሸባሪው ሕወሃት ኅይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመለሱ ጫና እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ።

አንዳንድ የውጪ ኃይሎች የሽብር ቡድኑን በመደገፍ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከሚያደርጉት ጣልቃገብነት እጃቸውን በመሰብሰብ የሰላም መንገድን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርቧል።

53 ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ቆሞ ሰላማዊ አማራጮች እንዲቀጥሉ ሲል የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የአቋም መግለጫውን ያነበቡት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብርሃቱ አለሙ እንዳሉት፤ ለረጅም ዘመን በዘለቀ ጦርነት ስልጣኔና ዕድገቷ የተገታው ኢትዮጵያ አሁንም ከጦርነት አዙሪት አልወጣችም።

ባለፉት 22 ወራት ገደማ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ አኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ማስከተሉን ጠቅሰዋል።

ይህ አውዳሚ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የህዝብ ጽኑ ፍላጎት እንደነበርም ተናግረዋል።

የጦርነቱ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት መጠነ ሰፊ ስራዎች ቢከናወኑም ከጉዳቱ ስፋትና ክብደት አንጻር በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ስራው የሚፈለገውን ያክል አለመሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ለወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔና ጦርነቱ ሰላማዊ እልባት እንዲሰጠው በአፍሪካ ሕብረት በኩል የተጀመረው ጥረት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር አንስተዋል።

ሰላማዊ አማራጩ እያለ በወርሃ ነሃሴ በአሸባሪው ሕወሃት ኅይሎች በተከፈተው ጥቃት ሳቢያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ምክር ቤቱን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ 'ለኢትዮጵያ የሚበጀው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት ነው' ብሎ እንደሚያምን ገልጸው፤ አሁንም ቢሆን በሰላማዊ ውይይት፣ ምክክርና  መግባባት ችግሮች እንዲፈቱ ምክር ቤቱ ጠይቋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ጥቃቱን የጀመሩት የአሸባሪው ሕወሃት ኃይሎች መንግስት በወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃ መሰረት ወደ ሠላም አማራጭ እንዲመለሱ ጠይቋል።

አሸባሪው ሕወሃት ለትግራይ ሕዝብ ሠብዓዊ ዕርዳታ የቀረበን ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም መዝረፉ የትግራይን ህዝብ ለችግር የሚዳርግ ነውረኛ ተግባር መሆኑን ጠቅሶ አውግዟል።

የውጪ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከሚያደርጉት ጣልቃገብነት እጃቸውን እንዲሰበስቡ፣ ይልቁንም  የሰላም መንገድን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።

መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ኅላፊነት ስላለው በቅርቡ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ በገባ የጠላት አውሮፕላን ላይ የተወሰደውን እርምጃ ምክር ቤቱ አድንቋል።

ለኢትዮጵያ ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት ሁሉም የሚዲያ ተቋማትና ዜጎች ጦርነትን ከሚያባብሱ መልዕክቶችና ተግባራት ተቆጥበው በሠላም አማራጭ ላይ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል።

የአለም አቀፉ የዲፐሎማቲክ ማህበረሰብ የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ጦርነቱ እንዲቆም፣ ሰላማዊ ውይይትና ንግግር በሚጀምርበት ሁኔታ በገለልተኝነት አጋርነታቸዉን እንዲያሳዩና በአሸባሪው ሕወሃት ኅይሎች ላይ ጫና እንዲያድርጉ ጠይቋል።

የእርስ በርስ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በአገር ደረጃ እንደመፍትሄ የተጀመረው አገራዊ ምክክር  እንዲጠናከር ምክር ቤቱ እንደሚደግፍም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም