አሸባሪው የህወሃት ቡድን በቆቦ ወረዳ ህፃናትና አዛውንቶች ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈፅሞብናል-ተጎጂዎች

149

ነሐሴ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ)አሸባሪው የህወሃት ቡድን በቆቦ ወረዳ ህፃናትና አዛውንቶች ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈፅሞብናል ሲሉ የጥቃቱ ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ገለጹ።

የሽብር ቡድኑ ለሰላም የተሰጠውን እድል ትቶ ጦርነት በከፈተባቸው የአማራ ክልልና አፋር ክልል ወረዳዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ የሽብር ተግባር መፈጸሙን አሁንም ቀጥሏል።

የትግራይ ህጻናትና ወጣቶችን በህዝብ ማዕበል አሰልፎ ወረራ የፈጸመው የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ በሚገኙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ከቀናት በፊት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል።

ንፁሃንን በመጉዳት የተካነው የሽብር ቡድኑ በቆቦ ወረዳ የአርሶ አደሮችን ቤት በመድፍ በመደብደብ በህፃናትና አዛውንቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑ ነሐሴ 19 ቀን 2014 በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ አቶ ደሳለ ትኩየ የተባሉ የ60 ዓመት አዛውንትና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።

የከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈጸም ከብቶችን በመጠበቅ ላይ የነበሩ ታዳጊዎችን ለከባድ የአካል ጉዳት ዳርጓል።ህክምና እየተከታተሉ ያገኘናቸው ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው የሽብር ቡድኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት በንጹሃን አርሶ አደሮችና በታዳጊዎች ላይ ለከባድ የአካል ጉዳት የዳረገ ጥቃት እንደፈጸመባቸው ተናግረዋል።

"እኛ አርሶ አደሮች ነን፤ የሽብር ቡድኑ በማዕበል ወረራ ፈፅሞ ዘረፋ መፈጸሙ ሳያንስ በከባድ መሳሪያ ደብድቦናል" ይላሉ።

ምንም የማያውቁ ህጻናት ከብቶችን እየጠበቁ ባለበት ወቅት በከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈጸም ለህጻናት የሚራራ ልብ እንኳ እንደሌለው በተግባር ማሳየቱንም እንዲሁ።

የሽብር ቡድኑ ያደረሰባቸው ጉዳት መቼም የማይሽር ጠባሳ መሆኑን የገለጹት ተጎጂዎቹ፤ በአሁኑ ወቅት ተገቢ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆኖም በሽብር ቡድኑ ወረራ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን በህይወት የመኖርና አለመኖር ሁኔታ አለማወቃቸው በእጅጉ እንዳሳሰባቸውም ነው የተናገሩት።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የትግራይን ህጻናት ለደም ግብሩ ከፊት በማዕበል በማሰለፍ ወረራ እየፈጸመ በንጹሃን ላይ ጥቃት በመፈፀም በዚህም በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ የሽብር ወንጀሉን ቀጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም