ምርጫ ቦርዱ በተያዘው በጀት ዓመት አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ መታቀዱን አስታወቀ

84

ነሐሴ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2015 በጀት ዓመት በሀገሪቱ አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ መያዙን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመተባበር  አካባቢያዊ ምርጫን በሚመለከት ከፖለቲካ ፓርቲዎች  የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና ግብአት ለመሰብሰብ የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አካባቢያዊ ምርጫን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ሲያደርግ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በዚህም በሁሉም ቦታዎች አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ክልሎች የሚያደርጉትን ቅድመ -ዝግጅት መሰረት በማድረግ ምርጫው እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

 ምርጫ ቦርድም ይህን አካባቢያዊ ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አካባቢያዊ ምርጫ ትክክለኛ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በየክልሉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አቶ ፈይሰል አብዱልአዚዝ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በሀገሪቱ ለማካሄድ የታሰበው አካባቢያዊ ምርጫ ወደ 53 የሚጠጉ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ዋና ፀሀፊ ለገሰ ላንቀሞ አካባቢያዊው ምርጫ የተሳካ እንዲሆን እና ህብረተሰቡ የሚወክለውን አካል  እንዲመርጥ  ፖለቲካ ፓርቲዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ ስራ ላይ በመሰማራት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ መስራት እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም