ከማዕድን ሀብት የተሻለ ገቢ ለማግኘት ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ ተጀምሯል---የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

94
አዳማ መስከረም 8/2011 በሀገሪቱ ከማእድን ሀብት እየተገኘ ያለውን ዝቅተኛ ገቢ ለማሻሻል የተቋማዊ ሪፎርም ትግበራ መጀመሩን  የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ። የማዕድን፣ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የ2010 በጀት አመት የሥራ አፈጻፀምና የ2011 በጀት አመት እቅድ ላይ ያተኮረ የዘርፍ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት የምክክር መድረክ ከትላንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው ። ሚኒስትሩ አቶ መለስ አለሙ እንደገለፁት በሀገሪቱ በተለይም ባለፉት ሶሰት አመታት ከማእድን ሀብት እየተገኘ ያለው ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ የሪፎርም ትግበራ ማካሄድ አስፈልጓል ። "የማዕድን ዘርፍ ተቋማት አደረጃጀትና አሰራር በህግ ማአቀፍ ያልተደገፉ መሆንና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎችን ወደ ዘርፉ በማስገባት ላይ የሚታየው የአፈጻፀም ከፍተት ከዘርፉ እየተገኘ ላለው ገቢ ዝቅተኛ መሆን ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው " ብለዋል ። በዘርፉ የሚስተዋሉ የኮንትሮባድና ህገወጥ ንግድ እንቅሰቃሴም ለገቢው መቀነስ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል። ከዘርፉ የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሪ ባለመገኘቱ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩን ገልፀዋል ። በተለይም ዘርፉ የራሱ የሆነ ዝርዝር የህግና የፖሊሲ ማእቀፍ አለመኖር፣ወጥ የሆነ የአደረጃጀትና አሰራር ክፍተት፣በቴክኖሎጅ የታገዘ ዘመናዊ አሰራር አለመዘርጋትና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ካለፈው አመት ጀምሮ ተቋማዊ ሪፎርም ትግበራ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የታዩ ድክመቶችን በመለየት በተያዘው በጀት አመት ውጤታማ ሥራ ለመስራትና የተጀመረውን ሪፎርም ማጎልበት የሚያስችል የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ  የመድረኩ አላማ ነው። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእቅድና ክትትል ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገረመው ነጋሳ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት 33ሺህ 692 ኪሎግርም ወርቅ ለማእካላዊ ገበያ በማቅረብ 1ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ። "ማቅረብ የተቻለው 6ሺህ 747 ኪሎግራም ብቻ በመሆኑ ገቢም 225 ሚሊዮን ዶላር ሊሆን ችሏል" ብለዋል ። በባህላዊ አምራቾችና በኩባንያዎች ተመርቶ ለገበያ የቀረበው  የወርቅ መጠን ከእቅዱ እንጻር አፈጻጸሙ 25 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል ። በሌሎች የግንባታና የከበሩ ማዕድነት በተለይም ታንታለም፣ እምነበረድ፣ እሴት ከተጨመረበትና ከጥሬ ኦፓል ተመሳሳይ ዝቅተኛ አፈፃፀም መመዝገቡን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ ከዘጠኙ ክልሎች የዘርፍ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና የሥራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም