የውጭ አገር የስራ ስምሪት በዚህ ወር መጨረሻ ሊጀመር ነው

219
አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 ለአመታት ታግዶ የነበረው ህጋዊ የውጭ አገሮች የስራ ስምሪት ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑ በ2011 ዓ ም መስከረም ወር መጨረሻ እንደሚጀመር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት የውጭ አገር የስራ ስምሪት ዝግጅት ሊዘገይ የቻለው ስምሪት ከሚደረግባቸው አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የመፈራረም ሂደቱ ዘግይቶ ስለነበር ነው። ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ መፈረማቸውንም ጠቁመዋል። ስምምነቱ ተቀባይ አገሮች የዜጎችን ደህንነት ፣ ክብርና መብት እንዲጠብቁና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ዜጎች ኢንሹራንስ እንዲኖራቸውና በየአገሮቹ ካሉ የኢትዮጵያ ተወካዮች ክትትልና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሀሳቦች በስምምነቱ እንዲካተት መደረጉን ገልጸዋል። ለስራ የሚጓዙ ዜጎች ስለሚሄዱበት አገርና የስራ ዘርፍ አስፈላጊው ስልጠናና ድጋፍ የመስጠት ስራ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ተቀባይ አገሮች በሚገቡት ውል መሰረት ዜጎችን ለመቀበልና ውሉን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በጋራ ለመስራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ህጋዊ የስራ ስምሪትን ለማሳለጥ ከሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር ባሻገር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራትን የሚጠይቅ በመሆኑ ተቋማት ለህጋዊ ጉዞ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የጠየቁት አምባሳደር ምስጋኑ ውል ከገቡ አገሮች በተጨማሪ ከሌሎች አገሮች የውል ለመፈራረም ድርድር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ዓ.ም በየካቲት 2008 ዓ.ም ጸድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም