ህዝቡ ጦርነቱን ለመመከት የደጀንነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል--- የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር

75

ደሴ (ኢዜአ) ነሐሴ 26/2014 አሸባሪው ህወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ተደራጅቶ የደጀንነት ሚናውን እንዲወጣ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ጥሪ አቀረበ።

በህወሓት ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ አካባቢያቸውን ለቀው በዞኑ የተጠለሉ ወገኖችም ወደቄያቸው እየተመለሱ መሆኑንም አስታውቋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በፊት ንጹሀንን በመጨፍጨፍና የሀገር ሀብት በማውደም የፈጸመው ግፍ አልበቃው ብሎት ዳግም ጦርነት ከፍቷል።

በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ የጀመረውን ጦርነት ለመመከትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አመራሩም ከህብረተሰቡና ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ ዛሬም የደጀንነት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

"የአካባቢውን ሰላም በቅንጅት ከመጠበቅ ባለፈ፣ ለወገን ጦር ስንቅ በማዘጋጀትና በተለያየ መንገድ አለኝታነቱን ዳግም ማሳየት አለበት" ብለዋል።   

በአሁኑ ወቅት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያለው አመራር ህዝቡን ከማስተባበር ጎን ለጎን በአሸባሪው ህወሓት ሀሰተኛ ወሬ ግራ እንዳይጋባ የግንዛቤ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሀሰተኛ ወሬ ተረብሸው አካባቢያቸውን ለቀው በዞኑ የተጠለሉ ወገኖች ወደቄያቸው እየተመለሱ መሆኑንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በተለይ ከወልዲያ፣ መርሳ እና ሌሎች አካባቢዎች የመጡ ወገኖች ወደቤታቸው እየተመለሱ  መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱ፣ "ህብረተሰቡ ከልማት ሥራው ጎን ለጎን ሰላሙን ሊያጠናክር ይገባል" ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ለስልጣን ሲሉ ህዝብ የሚያስጨፈጭፉ ጥቂት የህወሓት አመራሮችን በቃችሁ በማለት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መቆምና ነጻነቱን ማወጅ እንዳለበትም ገልጸዋል።

የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ መስኡድ አበራ በበኩላቸው፣ "ህብረተሰቡ ተረጋግቶ አካባቢውን በጋራ እንዲጠብቅና የሽብር ቡድኑን ሴራ እንዲያከሽፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

"ወጣቱን ከማደራጀት ባለፈ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና አንድነቱን እንዲያጠናክር በማድረግ የህወሓትን ፕሮፖጋንዳ የማክሸፍ ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል።

አቶ መስኡድ እንዳሉት፣ በውሸት ወሬ ተደናግጠው ወደሐይቅ ከተማ የመጡት የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ወደቄያቸው መመለስ ጀምረዋል።  

ወደከተማው ሠርገው የገቡትን የጥፋት አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ከመንግስት ጎን በመሆን የካባቢያችንን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ለሠራዊቱ ደጀን ለመሆን ዝግጁ ነኝ'' ያሉት ደግሞ፣ የሐይቅ ከተማ ነዋሪ አቶ ታሪኩ ታምራት ናቸው።

"በውሸት ወሬ አካባቢያችንን አንለቅም፤ ይልቁንም ጠላትን በግንባር ለመፋለም ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ወደአካባቢያቸው ሰርገው የገቡ ተላላኪዎችንም እያጋለጡ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሌላው የሐይቅ ከተማ ነዋሪ አቶ ሞገስ መላኩ በበኩላቸው፣ "የሰላም አማራጮችን ረግጦ ጦርነት ለከፈተ የሽብር ቡድን አንበረከክም፣ አንድነታችንን በማጠናከር የኢትዮጵያን ትንሳኤ እናቀርባለን" ብለዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን የልማት ሥራውን አጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም