በአማራ ክልል ሁለት ከተሞች ለሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች የጽሕፈት መሳሪያ ድጋፍ ተደረገ

57
ደብረማርቆስ/ደብረብርሀን መስከረም 8/2011 የተደረገላቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የ2011 ትምህርት ዘመን ተረጋግተው በመማር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዛቸው በደብረ ማርቆስና በደብረ ብርሃን ከተሞች ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች ገለፁ። በደብረ ማርቆስ ከተማ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዋ ብርሃን ውበት ለኢዜአ እንደገለፀችው ለ2011 የትምህርት ዘመን የተደረገልኝ ድጋፍ ያጋጥመኝ ከነበረው የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ስለታደገኝ እንደማንኛውም ተማሪ ትምህርቴን እንድከተታል ያስችለኛል ። ከዚህ በፊት በየአመቱ የመማሪያ ቁሳቁስና የዩኒፎርም ችግር ያጋጥማት ስለነበር የቀን ስራ በመስራት  ወጪዋን ትሸፍን እንደነበር አስታውሳ ድጋፉ ይሄንን ችግሯን እንዳቃለለላት ተናግራለች። ሌላው የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ዮሃንስ ዘላለም በበኩሉ የመማሪያ ደብተር እና እስክርቢቶ በማግኘቱ ትምህርቱን በሚገባ እንደሚከታተልና ጥሩ ውጤት ለማምጣትም ጠንክሮ እንደሚማር ተናግሯል። እናቱ  የሰው ቤት እየሰሩ የሚተዳደሩ ስለሆነ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ከባድ መሆኑን ገልጾ በዚህ አመት የተደረገለት የቁሳቁስ ድጋፍ እናቱን ከማስቸገር ተላቆ በተሟላ መንገድ ለመማር እንደሚያስችለው አመልክቷል። የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሪት ብሩክታይት አሰፋ እንደገለጹት ችግረኛ ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይደናቀፉ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት ኮሚቴን በማጠናከር ችግሩን ማቃለል እየተቻለ ነው። ተስፋ የልማት ማህበር እና ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት የተባሉ ድርጅቶች ከሦስት ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች እንደ ክፍል ደረጃቸው ከ5 እስከ 12 ደብተር እና ሁለት ሁለት እስክሪብቶ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ድርጅቶቹ 240 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ የገዛውን የደብተርና እስክሪብቶ ድጋፍም ተማሪዎች ያለስጋት ትምህርታቸው ላይ አንዲያተኩሩ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው የሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ሰራተኞች እና የሸዋ አማራ ወጣቶች ማህበር ለችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች 200 ሺህ ብር ግምት ያለው የትምህርት ቁሳቁስ አበርክተዋል። የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ኮማንደር እንደሻዉ ማሙየ እንደገለጹት በማረሚያ ቤቱ አባላት መዋጮ ሶሰት ህፃናትና አንድ አረጋዊያን በወር ስድስት መቶ ብር ለቀለብና ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሰ በቋሚነት ሲደግፍ  መቆየቱን ተናግረዋል። በቋሚነት ከሚደገፉ ተማሪዎች በተጨማሪ አዲሱን የትምህርት ዘመን በማስመልከት 35 ሺህ ብር ግምት ያለው ለ100 ህፃናት የመማሪያ ደብተር፣ እስክሪብቶና ቦርሳ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። የሸዋ አማራ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ፍቅረ ሽመልስ በበኩሉ 164 ሺህ 500 ብር ግምት ያለው እስክሪቢቶና ደብተር ከ4ኛ ክፍል በታች ላሉ ችግረኛ ህፃናት እንዲደርስ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ማስረከባቸውን ተናግሯል። በቀጣይም ማህበሩ በአዳማ ፣ በቢሾፍቱና አዲስ አበባ ለሚገኙ 240 ችግረኛ ህፃናት ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቋል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደረጀ ጌታነህ በበኩላቸው "ማህበሩ የጀመረው ድጋፍ በቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው የሚያቋርጡ ህፃናትን ቁጥር በመቀነስ እኩል ተሳትፎና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ይረዳል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም