በአዲስ አበባ የቧንቧ ውሃ ተበክሏል በሚል የተናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው

59
አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 በአዲስ አበባ ከተማ  የቧንቧ ውሃ ተበክሏል በሚል በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የመዲናዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ባለስልጣኑ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከግድቦችና ከማሰራጫ ቦታዎች ናሙና በመውሰድ የከተማዋ ውሃ ላይ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል። ይኸው ፍተሻ ትናንትና በ30 ቦታዎች፤ ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ 30 ቦታዎች ተደርጓል፤ በዚህም ለከተማዋ የሚደርሰው ውሃ በአስተማማኝ ሁኔታ ንጽሕናውን የጠበቀ መሆኑ መረጋገጡን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ እየተናፈሰ ያለው መረጃ የፈጠራ ወሬና ከእውነት የራቀ በመሆኑ ሕብረተሰቡ እንደወትሮው ያለምንም ስጋት የቧንቧ ውሃ መጠቀሙን እንዲቀጥል አሳስበዋል። ሕብረተሰቡ እንዲህ አይነትና ሌሎች መረጃዎች ሲኖሩ ህብረተሰቡ በነጻ የስልክ መስመር 906 ደውሎ ማሳወቅ ወይም በአቅራቢያ በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በአካል ቀርቦ በማሳወቅ እንዲጣራ ማድረግ እንደሚቻልም አቶ እስጢፋኖስ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም