የንግድ ሚኒስቴር ላኪዎች የገቡትን ውል አክብረው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲችሉ እየተሰራ እንደሆነ ገለጸ

87
አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 የኢትዮጵያ ላኪዎች ውል አክብሮ ምርቶችን የመላክ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከተጣለበት ኃላፊነት አንዱ ወደውጪ ለሚላኩ ምርቶች ገበያ ማፈላለግ ሲሆን በ2010  ላኪ ድርጅቶች ከውጪ ድርጅቶች ጋር  በማስተሳሰር የ50 ሚሊዮን ዶላር የገበያ ውል ተገብቶ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከአገር ለሚወጡ ምርቶች ሽያጭ ውል በኢትዮጵያ ላኪዎችና በውጪ ተቀባይ ኩባንያዎች መካከል ቢፈረምም በስምምነቱ መሰረት በሚፈለገው ጥራት፣ ጊዜና መጠን ምርት ማቅረብ ባለመቻሉ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በዕቅዱ መሰረት አልተከናወነም። በውል የሚደረግ ሽያጭ በላኪዎችና በውጪ ተቀባይ ኩባንያዎች ዘንድ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ ውሉን በማስፈጸም ረገድ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። ውልን አክብሮ አለመስራት በተቀባዩ ዘንድ ያለውን እምነት እንዲሸረሸር በማድረግ በኤክስፖርቱ ላይ ስጋት እንደሚሆን ተናግረዋል። የገበያ ትስስሩ የተገኘው 4 ሺህ 195 ኩባንያዎች ተሳታፊ በሆኑባቸው በአገር ውስጥ በተካሄዱ ሁለት ኤግዚቢሽኖችና በውጪ አገሮች በተከናወኑ አስር 'ትሬድፌይሮች' አማካኝነት ነው ተብሏል። 'በውል አፈፃፀም ላይ የታዩ 12 ማነቆዎችን ፈትቻለሁ' ያለው ሚኒስቴሩ የውል ግዴታቸውን አክብረው መፈፀም ባልቻሉ ኢትዮጵያውያን ላኪዎች ላይም የገቡትን ስምምነት እንዲፈፅሙ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጿል። ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ በዘላቂነት ለመፍታትና የአገርን ገፅታ ለማስጠበቅ በ2011 ዓ.ም አዲስ አሰራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አቶ መላኩ ገልፀዋል። ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ አሰራር በገቡት ውል ግዴታቸውን በማይወጡ ላኪዎች ላይ የህግ አስገዳጅነትን የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም