ኢትዮጵያ ለሎጂስቲክስ ወጪ የምታደርገውን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማስቀረቱን የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ማህበር ገለጸ

152

ነሐሴ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ለሎጂስቲክስ ወጪ ልታደርግ የነበረውን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ማስቀረቱን የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ገልጿል።

የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ ለኢዜአ እንዳሉት የባቡር ትራንስፖርት የሚሰጠው የጭነት አገልግሎትና የመንገደኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ በ2014 በጀት ዓመት በባቡር ትራንስፖርት አማካይነት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን በላይ የወጪና ገቢ ንግድ ጭነቶችን ማጓጓዝ ተችሏል።

የአፈር ማዳበሪያ፣ስንዴ፣ብቅልና የምግብ ዘይት በዋናነት የተጓጓዙ የጭነት አይነቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።በበጀት ዓመቱ በተመሳሳይ ከ71 ሺህ በላይ ኮንቴነሮችን ያጓጓዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ የሚሆነው የወጪ ንግድ ኮንቴነር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው የቡና ምርት 98 በመቶ የሚሆነው በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አማካኝነት እንደተጓጓዘም ተናግረዋል።የባቡር ትራንስፖርት በሰጣቸው የጭነት ማጓጓዝ አገልግሎቶች ኢትዮጵያ ለሎጂስቲክስ የምታወጣውን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ማስቀረት መቻሉን ጨምረዋል።

ዶክተር አብዲ አክለውም የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት መስጠት ከሚችለው የአገልገሎት አቅሙ እስካሁን እየተጠቀመ ያለው ከ35 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የሚሰጣቸውን የአገልግሎት አይነቶች ለማስፋት መዘጋጀቱን አብራርተው በቅርቡ ነዳጅን ጨምሮ አዳዲስ የምርት ጭነቶችን ለማጓጓዝ እቅድ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር መስመር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።በ2014 በጀት ዓመት በሰጣቸው የህዝብ ትራንስፖርት አገልገሎቶች ከ155 ሺህ በላይ መንገደኞችን ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች አጓጉዟል።

በታዳሽ ኃይል የሚሰራ የባቡር አገልግሎት በመስጠት በበጀት ዓመቱ 61 ሺህ ቶን የካርበን ልቀትን ወደ ከባቢ አየር ከመልቀቅ ማስቀረት ተችሏል።

ከስራ እድል ፈጠራ አንጻር ለ2 ሺህ 891 ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን 2 ሺህ 431 ኢትዮጵያውያን፣ 460ዎቹ ደግሞ የጅቡቲ ዜጎች ሲሆኑ በባቡር መጠገን፣ ማሽከርከር፣ የባቡር ኦፕሬሽን ዲዛይን ማድረግና ሌሎች የባቡር ቴክኖሎጂ እውቀት ማዳበር ችለዋል።

በኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚተዳደረው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር የውስጥ አቅምን ማሳደግና ትርፋማነትን ማሳደግ የቀጣይ ዋና ዋና ትኩረቶቹ መሆናቸውን ገልጿል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ስራ ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአስራ ዘጠኝ የባቡር ጣቢያዎቹ የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም