ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ በተለቀቀ ኬሚካል የጓሮ አትክልትና ሰብል ወድሞብናል- የደብረብርሀን ከተማ አርሶ አደሮች

74
ደብረብርሃን መስከረም 7/2011 ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ የተለቀቀ ኬሚካል የተቀላቀለበት ፍሳሽ የጓሮ አትክልትና ሰብላችንን ጎድቶብናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ። ፋብሪካው በበኩሉ ለአርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ ለመፈፀም በማሳ ላይ የደረሰው ጉዳት በባለሙያ እየተጠና መሆኑን አስታውቋል ። በደብረብርሃን ከተማ የቀበሌ 09 ነዋሪ አርሶ አደር ማሙሽ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ከፋብሪካው ተጣርቶና ታክሞ የሚለቀቅ ፍሳሽን ለመስኖ ልማት ሲጠቀሙ ቆይተዋል ። "ይሁን እንጂ ባለፈው አመት በጋ ወቅት ድንገት የተለቀቀ ኬሚካል የተቀላቀለበት ፍሳሽ  በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ የተከልኩትን ካሮት ሙሉ ለሙሉ አውድሞብኛል" ብለዋል ። በዚህም ከ150 ኩንታል በላይ የካሮት ምርት ማጣታቸውን ሲገልጹ የተፋውን ገልብጠው ዳግም የዘሩት ገብስም ሊበቅል እንዳልቻለ ተናግረዋል ። "ቤተሰቤን የማስተዳድርበት ትርፍ ስራ ስለሌለኝ ለችግር ተዳርጌያለሁ" ብለዋል። ከፋብሪካው ድንገት የተለቀቀ ኬሚካል የተቀላቀለበት ፍሳሽ በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረን የካሮት ተክል እንዳወደመባቸው የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር እንዳለ ገብረእግዚአብሄር ናቸው ። "ለማሳው በአመት 10ሺህ ብር ኪራይ እየከፈልኩ አትክልትና ሰብል እያፈራረኩ በመዝራት አምስት ቤተሰቦቼን ሳስተዳድር ቆይቻለሁ" ያሉት አርሶ አደር እንዳለ ሰብላቸው ላይ ለደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል ። አርሶ አደር ግዛዉ ሽዋዬ በበኩላቸው በፍሳሹ ጉዳት ከደረሰበት ማሳቸው የሚጠብቁትን 80 ኩንታል ድንችና ካሮት ምርት ማጣታቸውን ተናግረዋል ። "በመኽር ወቅቱ በማሳው ላይ የዘራሁት የገብስና የስንዴ አዝመራም እንደወትሮው ሊበቅል ባለመቻሉ ከነቤተሰቦቼ ለችግር ተጋልጠናል" ብለዋል። በሰብላቸው ላይ ለደረሰው ጉዳት ፋብሪካው ካሳ እንዲከፍላቸው አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል ። የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና፣ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መልሶ ማቋቋም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አውራሪስ አረጋ  ከፋብሪካው ታክሞ የሚለቀቅ ፍሳሽን አርሶ አደሩ ለመስኖ በማዋል የጓሮ አትክልት እያመረተ ተጠቃሚ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል ። ባለፈው ዓመት በጋ ወቅት በድንገት ተለቀቀ በተባለው ያልታከመ ፈሳሽ በ32 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በነበረ የጓሮ አትክልትና ሰብል ላይ ለደረሰው ውድመት የካሳ ክፍያ እንዲፈፀም የጉዳት መጠኑ እየተጠና መሆኑን ጠቁመዋል ። የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ ዝቄ በበኩላቸው ከፋብሪካው የሚለቀወቀውን የታከመ ውሃ አርሶ አደሮች ለመስኖ ልማት ይጠሙ እንደነበር ተናግረዋል ። "ድንገት በተለቀቀ ፈሳሽ በማሳ ላይ በነበረ የጓሮ አትክልት ላይ ጉዳት ደርሷል" ያሉት ስራ አስኪያጁ ፋብሪካው የህዝብ ሃብት በመሆኑ ለአርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ ለመፈፀም በሰብል ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን በባለሙያ እየተጠና መሆኑን ተናግረዋል ። "ከፋብሪካው ያልታከመ ፍሳሽ አምልጦ የወጣበት ምከንያት እየተጠና ነው" ያሉት ስራ አስኪያጁ አርሶ አደሩ ተጣርቶ በሚለቀቅ ፍሳሽ በዘላቂነት የሚጠቀምበት መንገድ እንደሚመቻች አመላክተዋል ። በዳሽን ቢራ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኙ ከ89 በላይ አርሶ አደሮች ከፋብሪካው ታክሞ የሚለቀቅ ፍሳሽን ለመስኖ እንደሚጠቀሙ ታውቋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም