''አለም የሚደመምበትን የቅዱስ ላልይበላ ኪነ-ህንፃ ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ ሃላፊነት አለበት'' ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

108

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)''አለም የሚደመምበትን የቅዱስ ላልይበላ ኪነ-ህንፃ ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ ሃላፊነት አለበት'' ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

በላልይበላ ከተማ አስተዳደር የላስታ ላልይበላ የአሸንድዬ ሆያሆዬ በዓል በደመቀ መልኩ እየተከበረ ነው።

አቶ ደመቀ መኮንን በበዓሉ ላይ እንዳሉት በሃገራችን እንቁ ከሆኑት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ውስጥ ላልይበላ ዋነኛው ነው።

ላስታ ላልይበላ ካለው ጥንታዊ ኪነ ህንፃ ባሻገር ድንቅ የሆኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል ባለቤት ነው ሲሉም ገልፀዋል።በዚህም አለም የሚደመምበትን የቅዱስ ላልይበላን ኪነ ህንፃ ታሪካዊነቱን ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያቶች ባለፉት ሁለት አመታት ሳይከበር ያለፈውን የአሸንድዬ በዓል እንዲከበር ለነፃነት ዋጋ የከፈሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የላልይበላን ኪነ ህንፃ አደጋ ተጋላጭነት እንዳይስፋፋና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍም የፌደራሉ መንግስት፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣የክልሉ መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት ይሰራል።

ከአባቶቻችን የወረስነውን ድንቅ ባህልና ኪነ ጥበብ የአሁኑ ትውልድም የበለጠ እንዲሰራበትም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።

የላልይበላን የአለም ቱሪስትነቱን ባስጠበቀ መልኩ ለማጠናከር የፌደራል መንግስቱ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤የላልይበላ ከተማ ነዋሪም ለቱሪዝም ዘርፉ የሚመጥን ተግባር ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

May be an image of 4 people, people standing and outdoors

የፌደራሉ መንግስት ለሰላም አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀው ሃገራችንን ለሚዳፈሩ ግን መላ ኢትዮጵያዊያን እንደ አባቶቻችን አንድነትን በማጠናከር የሃገራችንን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ይገባል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የአሸንድዬ በዓል በደመቀ መልኩ መከበሩ የኢትዮጵያን የመጭው ግዜ ብሩህነት አመላካች ነው።

መንግስት ድህነትን ለመቅረፍ ዋነኛ አማራጩ ሰላም መሆኑን በመረዳት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ለአንድነትና መተባበር ትልቅ ዋጋ በመስጠት የአሸንድዬ በዓልን የአለም መዳረሻ ለማድረግ ክልሉ አበክሮ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባንታብል በበኩላቸው የአሸንድዬ በዓል የአብሮነት፣የአንድነትና የነፃነት ተምሳሌት በዓል ነው።

የአሸንድዬ በዓልን ለተተኪው ትውልድ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲሸጋገርም ዞኑ ይሰራል ሲሉ ገልፀዋል።በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ የፌደራል፣የክልሉና የዞኑ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችና የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም