ወጣቶች የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ ለማበላሸት የሚሰሩ ሃይሎችን ሴራ በመታገልና አብሮነትን በማጽናት በአገር ግንባታ ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

118

ነሐሴ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቶች የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ ለማበላሸት የሚሰሩ ሃይሎችን ሴራ በመታገልና አብሮነትን በማጽናት በአገር ግንባታ ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

በመድረኩ ወጣቶች ከመልካም አስተዳደር፣ ስራ አጥነት፣ የሰላምና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

ወጣቶቹ ለውጡን ተከትሎ የተገነቡ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ብሩህ  መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣቶቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ብታልፍም ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የገበታ ለአገር፣ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶችና መንገድን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

እነዚህ የልማት ስራዎች ለወጣቶች ተስፋ የሰነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ወጣቶች አብሮነታቸውን ጠብቀው በተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል ብለዋል።

መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግር መሰረት የሆነውን ሌብነት ለመከላከል በተደራጀ መልኩ ጠንካራ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ነው ያረጋገጡት።

የበጎ ፈቃድ አገልሎትን ከማጠናከር አኳያ ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ያላቸውን የእረፍት ጊዜ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው በፈቃደኝነት አገራቸውን የሚያገለግሉበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል።

ወጣቶች የነገ መፃኢ እድሎቻቸውን ለማበላሸት የሚሰሩ ሃይሎችን ሴራ በጋራ በመታገል የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባቱ ሂደት ላይ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም