በቡራዩ የተከሰተው ችግር ነዋሪዎቹን አይወክልም … ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

82
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በቡራዩ አካባቢ የተከሰተው ችግር የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደማይወክል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስታወቁ። ችግሩን የፈጠሩት አካላት የክልሉን ህዝብ ከሌላ ብሄር ጋር የማጋጨት ተልእኮ ያነገቡ አካላት ናቸው ብለዋል። የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የአካባቢውን አመራሮችና ወጣቶች በማወያየት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል። የቡራዩ ከተማ አቀማመጥ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ከግምት በማስገባት ወንጀለኞቹ መንቀሳቀሳቸውንም ጠቅሰዋል። ቀውስ ሲፈጠር ብዙ ጉዳቶች እንደሚደርሱ፣ነገር ግን ይህ ህዝባችንን አይወክልም ያሉት ዶከተር ነገሪ ህዝቡ ለወደፊትም ሰላሙን በጋራ እንዲጠብቅ አሳስበዋል። ችግሩን ማህበራዊ ሚዲያዎች እያባባሱት በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል። ችግሩ መፈጠሩ መረጃ እንደደረሰን ከአዲስ አበባ ፖሊስና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለናል ብለዋል። በደረሰን መረጃ መሰረት አስካሁን ከ 200 በላይ አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ የበላይነተን ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መንግስት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። የሞቱትንና የተፈናቀሉትን በተመለከተ በደረሰን መረጃ የ 23 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን የተፈናቀሉትን ነዋሪዎች ግን በቁጥር መለየት አልተቻለም ብለዋል። ቡራዩ አካባቢ ፣አስኮ መድኃኒአለም፣ኮልፌ አካባቢ የተሰባሰቡትን ወገኖች የፌደራል አደጋ ስጋትና የኦሮሚያ አደጋ ስጋት በጋራ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። የቡራዩና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተፈናቃዮቹ የሰፈሩበት ድረስ በመሄድ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑም ተጠቅሰዋል። በፌደራል ደረጃ የተለያዩ ኃላፊዎች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ መልሶ የማቋቋም ስራው በአጭር ጊዜ ይከናወናል ብለዋል። የደረሰውን ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደረስ ሚዲያዎች ኃላፊነት እንዳለባቸውና በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎች በዚህ ውስጥ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ በመሆኑ ህዝባችን መጠንቀቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም