በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የምናደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኢክናስ

154

ነሃሴ 14/2014/ኢዜአ/ የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ዜጎችን ለመርዳት በማሰብ የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) መቋቋሙ ይታወቃል።

ከተቋቋመ በኋላም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሕክምና ቁሳቁስ፣ የምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ የኢክናስ ምክትል ፕሬዝዳንት ማርቆስ ተገኝ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

መንግስት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማት የመልሶ ማቋቋም ስራ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ድጋፉን መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የኢክናስ አመራሮች በአማራና አፋር ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ቦታዎች ተዘዋውሮ በመመልከት የድጋፉን ሁኔታ በመገምገም ስራ መጀመሩን ያስታውሳሉ።

በዚህም ድርጅቱ በሁለቱ ክልሎች የወደሙ የግለሰብ ቤቶችን እያስገነባ እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በካናዳ በተለያየ ዘርፍ የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሙያዊ ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛሉም ብለዋል።

የቁሳዊ ድጋፍ ብቻ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን ሙሉ ስለማያደርገው ጦርነቱ በዜጎች ላይ ያደረሰውን ስነ ልቦና ቀውስም ማከም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም በካናዳ የሚገኙ የስነ ልቦናና ሌሎች ተጓዳኝ መስኮች የሚሰሩ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በካናዳ የሚኖሩ ወጣቶች የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን ለመደገፍ የበጎ ፈቃድ ስራ ለማከናውን ፍላጎት እንዳላቸውም ነው አቶ ማርቆስ የጠቆሙት።

ኢክናስ የመልሶ ማቋቋም ስራውን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅርቡ ውይይት ማድረጉንም ገልጸዋል።

“የኢክናስ ዋነኛ አላማ ለኢትዮጵያ መድረስና ኢትዮጵያውያንን መደገፍ ነው ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኘው ዳያስፖራዎች የመልሶ ማቋቋሙን ሂደት በገንዘብና በሙያ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ከተቋቋመበት ሕዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪና ለልማት ፕሮጀክቶች ከ5 ሚሊዮን በላይ የካናዳ ዶላር በገንዘብና በአይነት መለገሱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም