ወሎ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ ሚና ላበረከቱ 24 መምህራን የተባባሪና ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ሰጠ

125

ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወሎ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የጎላ ሚና ላበረከቱ 24 መምህራን የተባባሪና ረዳት ፕሮፌሰር እድገት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የተባባሪና ረዳት ፕሮፌሰር እድገቱን የሰጠው የላቀ ሚና ለተወጡ መምህራን ነው፡፡

እድገቱ የተሰጠውም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ትላንት ነሃሴ 12/2014 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ደረጃ እድገት ከተሰጣቸው 24 መምህራን መካከልም 21ዱ የረዳት ፕሮፌስርነት እድገት ሲሆን 3ቱ ደግሞ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

እድገቱ የተሰጠውም የህዝብን ችግር መሰረት በማድረግ በሰሩት ምርምርና ጥናት፣ በሰጡት ማህበረሰብ አገልግሎትና በሌሎች መለኪያዎች ብቁ ሆነ በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡

ተባባሪ ፕሮፌስርነት ማዕረግ የተሰጣቸው፡-

1. ዶክተር መታደል አዳነ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እና የዩኒቨርሲቲው የአቢሲኒያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጆርናል ዋና ኤዲተር ሲሆኑ ከ40 በላይ የምርምር ህትመት ስራቸውን በማቅረብ፣

2. ዶክተር ሰይድ ጌታሁን 14 የምርምር ህትመት ውጤቶችን በማቅረብ፣ በህክምና ሙያቸው ከፍተኛ የማህበረሰብ አገልግሎት በማበርከት፣ የውጭ ፕሮጀክት በማምጣት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግና ሌሎች ለደረጃ እድገቱ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በማሟላታቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

3. ዶክተር የሱፍ አህመድ በህክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የጽንስና ማሕፀን ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ሲሆኑ 10 የምርምር ህትመት ውጤቶችን በማቅረብና ለበርካታ አመታት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በመስራታቸው ማዕረጉ እንዲሰጣቸው ሴኔቱ መወሰኑን ገልፀዋል።

የረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ የተሰጣቸውም በተመሳሳይ በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠታቸው ሴኔቱ በመገምገም እድገቱ መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።