ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ከአይሳኢታ- አፋምቦ- ጀቡቲ ድንበር የአስፓልት መንገድ ግንባታ 71 በመቶ ላይ ደርሷል

103

ሰመራ፤ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ከአይሳኢታ- አፋምቦ- ጀቡቲ ድንበር እየተገነባ የሚገኘው የአስፓልት መንገድ 71 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ።

የመንገዱን ስራ በማማከር ላይ የተሰማራው የበይድዲያ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንት የግል ማህበር የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ምክትል ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጅነር ወንደሰን ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት የመንገዱ ግንባታ በነሐሴ ወር 2014 በ4 አመት ውስጥ ለማጠናቀቅ በ2011 ዓ.ም ነው የተጀመረው።

መንገዱ 49 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የአስፓልት ኮንክሪት መሆኑን ገልጸው ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከመንገዱ ስራ ውስጥ 35 ኪሎ ሜትሩ አስፓልት ለማልበስ ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ቀሪው የመንገድ ክፍል የአፈርና ተያያዥ ሙሌት ስራ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ቢታሰብም ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በወቅቱ አለመጠናቀቅና በሌሎች ምክንያቶች በመዘግየቱ አሁን ላይ 71 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የካሳ ጥያቄ ካለባቸው አካባቢዎች ውጭ የድልድይ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች በአብዛኛው እየተጠናቀቁ መሆኑን የገለጹት ተጠሪ መሃንዲሱ የመንገድ ሰራ በ2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የመንገዱ መገንባት በሀገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ አማራጭ የትራንስፖርት ኮሪደር በመሆን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

የአይሳኢታ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃቢብ አሊ ለመንገዱ ግንባታ ለሚፈርሱ 35 ቤቶች ሁለት ግዜ ግምት ቢሰራም በባለቤቶቹና በመንገዶች ባለስልጣን መካከል ከስምምነት ላይ አለመደረሱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ለሚፈርሱት ቤቶች አዲስ የዋጋ ግምት ተዘጋጅቶ ለባለስልጣኑ ለመላክ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባት ለከተማውና ለህብረተሰቡ እድገት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ይሰራል ነው ያሉት።

የአፋምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አሊ መንገዱ ለሀገር ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ጎን ለጎን በአካባቢው ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሀብትና ለም መሬት አልምቶ ለውጪ ገበያ በቀላሉ በማቅረብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

በመንገዱ ስራ ላይ እያጋጠሙ ያሉ የካሳ ጥያቄዎችንና የጸጥታ ችግሮችን መፍትሄ ለመስጠት ወረዳው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ግንባታው በአስር የመንገድ ሰራ-ተቋራጮች እየተሰራ ሲሆን የማማከር ስራውን ይዲድያ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንትሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አማካኝነት የሚሰራ መሆኑን ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም