መንግስት ፍትህን ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ኃላፊነትና ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ይወስዳል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

87
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 መንግስት ፍትህን ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲባል ኃላፊነትና ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ እንደሚወስድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። ጥፋትን በጥፋት ፈጽሞ ማረም እንደማይቻል የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደረሰው ጥፋት ምክንያት በዜጎች ውስጥ የሚፈጠር መጥፎ ስሜት ወደሌላ ጥፋት እንዳያመራ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል። ባለፉት ቀናት በቡራዩ፣ ከታና ሌሎች አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ድርጊት መንግስት በጽኑ የሚያወግዘው እንደሆነም ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዜጎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት ለመቅረፍና ጥፋተኞችን በማደን ለህግ ለማቅረብ የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የተቀናጀ ስምሪት መጀመራቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ደረጃ ችግሩ ሳይስፋፋና ሳይከፋ መከላከል የሚቻልበት ዕድል እያለ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አመራር አካላት በየደረጃው ተጣርተው በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉም ገልጸዋል። ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በከተማ አስተዳደሩና በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን በመጥቀስ በዘላቂነት መልሶ የማቋቋምና የተረጋጋ ህይወትን የማስቀጠል ተግባራት በትኩረት እንደሚከናወንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ''የጀመርነው የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እንቅስቃሴ ኃላፊነት የጎደለውና ህገወጥ ድርጊትን በፍጹም አያስተናግድም፤ ተቀባይነትም አይኖረውም'' ብለዋል። ''የህግ የበላይነት ያልነገሰበት ለውጥ በምንም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም'' ያሉት አቶ ደመቀ መንግስት የህግ የበላይነትንና ፍትህን ለሁሉም ለማረጋገጥ ኃላፊነቱን በተግባር እንደሚወጣ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም