የአፋር ክልል በኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው

125

ነሐሴ 12 ቀን 2014(ኢዜአ)በአፋር ክልሉ ባሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

ባለሃብቶችና የክልሉ መንግስት አካላት የተሳተፉበት ክልላዊ የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በሠመራ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን እንደተናገሩት፤ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የግል ባለሃብቱ ቁልፍ የልማት አጋር ነው።

በአፋር ክልል ካሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የእንስሳትና የማዕድን ሀብት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ክልሉ ለመሃል ሀገርም ሆነ ለወደብ ያለው ቅርበት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በቀላሉ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ምቹ ሁኔታ ወደ ተጨባጭ ልማት ለመቀየር የክልሉም መንግስት ባለሃብቱ መዋዕለ ነዋዩን አፍሰሶ ከእራሱ አልፎ ክልሉን ብሎም ሀገርን መጥቀም እንዲችል የአሰራር ማነቆዎችና በሂደት የሚገጥሙ ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በተለይም በአንዳንድ ወረዳዎች በጥቃቅን ምክንያቶች የባለሀብቱን ስራ ማስቆምና ማስተጎጓል መኖሩን ጠቅሰው፤ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው አስገነዝበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው ባለሀብቱ የሚያጋጠሙትን ችግሮች ፈጥነው ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ወይዘሮ ኤይሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ ያለኢንቨስትመንት እድገትና ልማት ሊረጋገጥ ስለማይችል ባለሃብቱ በየጊዜው የሚገጥሙት ችግሮች ለመፍታት ኮሚሽኑ ከባለሃብቱ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ለዚህም ተመሳሳይ የጋራ ፎረም ማድረግ በባለሃብቱና አስፈጻሚ አካላት መቀራረብን በመፍጠር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ባለሃብቱም በአዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ ክልሉንም ሆነ እራሱን ለመጥቀም መዘጋጀት እንዳለበትም አንሰተዋል።

ለዘመናት ህብረተሰቡ ሲጠቀምበት የኖረውን የወል አጠቃቀም ልማድ ለመቀየር ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ ለማስጨበጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ አካባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም ናቸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን ቢሮው ባለሃብቱና ቅሬታ አቅራቢዎችን በማወያየት እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈ በኢንቨስትመንት ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶችን ያለአግባብ በሚያስተጎጉሉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋልበፎረሙ መድረክ የተሳተፉ ባለሃብቶች አሉቡን ያሏቸውን ችግሮች አንስተው እንዲፈቱላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስት አካላትም የመፍትሄ ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሠመራ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም