የአስተዳደር ወሰኑ መካለል ለሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ቀጣይ ለሚሰራው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ጥሩ መሰረት የሚጥል ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

183

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአስተዳደር ወሰኑ መካለል ለሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ቀጣይ ለሚሰራው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ላይ በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ላይ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱም የአስተዳደር ወሰን መካለል ከዚህ ቀደም ሲነሳ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት፣የሕዝቦችን አብሮ የመኖርና በጋራ መልማት የሚያጠናክር መሆኑ ተመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ባለመኖሩ በተለይ መሰረተ- ልማት ዝርጋታና ወሳኝ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት እንዲሁም የመሬት ወረራን ጨምሮ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የአስተዳደር ወሰን መካለል የሕዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር፣ ዘላቂ የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ይህ የወሰን ማካለል ሂደት ተግባራዊ ሲደረግም የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት፣የኦሮሚያ ክልል ሕገ-መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር እንደመነሻ የተወሰደ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ይህም ለዘላቂ ሰላምና ልማት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

ሕዝባዊ የውይይት መድረኩን የመሩት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፤የአስተዳደር ወሰን መካለሉ ከአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ባሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ አሁን ይህ ወሰን ባለመኖሩ የሁለቱም ነዋሪ ሕዝቦች ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ትልቅ ስኬት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ከሕዝብ ይልቅ የመሬትን ሃብት ብቻ በማሰብ ያለፉት ሥርዓቶች በሁለቱም ወገን ባሉ ነዋሪዎች ላይ ዘርፈ- ብዙ ጉዳቶች ሲያደርሱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሥልጣን የያዘው መንግሥት ግን ለሕዝቡ የልማት፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሾችን በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የአስተዳደር ወሰን ጉዳይም የሕዝቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ ቆይቶ ምላሽ ማግኘቱን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ በሁለቱም ነዋሪዎች ላይ በደል ማድረስም ሆነ የዘረፋ ተግባር መፈጸም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

ውሳኔው ለሕዝቡ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ጠቁመው፤ በቀጣይ ለሚሰሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ታላቅ ሽግግር ይሆናል ብለዋል።

ውሳኔውን መሬት ለማስያዝና ለነዋሪው የሚሰጠው የቀደመው አገልግሎት እንዳይቆራረጥ የጋራ ጽህፈት ቤት እንደሚቋቋምም ጠቁመዋል።

ሕዝቡን በመሰረተ- ልማት ለማስተሳሰርም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን የማካለሉ ሥራ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም