በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶችን በስፋት ለዓለም አቀፉ ገበያ ለማቅረብ የሚረዳ ስምምነት ተፈረመ

110

ነሃሴ12/2014/ኢዜአ/ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች በዓለም አቀፉ ገበያ ያላቸውን ተፈላጊነት ለማጎልበት፣ ተደራሽነትን ለማስፋት፣የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣የሙያተኞችን ክህሎት ማዳበርና መሰል ጉዳዮችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ሃመን የምክር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው የተፈረመው።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች በሚፈለገው ደረጃ ለገበያ እንዲቀርቡና የሙያተኞችን ክህሎት ለማሳደግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ምርቶቹ የጥራት ደረጃቸውን በማሟላት በዓለም አቀፉ ገበያ ያላቸውን ተፈላጊነት ለማጎልበት የተደረገው ስምምነት የጎላ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት።

በተለይም አሜሪካ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን እድል ማንሳቷን ተከትሎ ወደ ሌሎች ሀገራት ምርት ለመላክ በጋራ መስራት የግድ ነው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ ከ125 በላይ የውጪና የሃገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች በፓርኮቹ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ካሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የማምረት አቅም አኳያ በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት እንደማይቻል  ገልጸዋል።  

በፓርኮቹ አልባሳትን ከሚያመርቱ ድርጅቶች ውስጥ ከ15 በላይ የሚሆኑት የጥራት ደረጃ ማረጋገጫ ያላገኙ በመሆናቸው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።

ስምምነቱ ድርጅቶቹ አስፈላጊው ፍተሻ ከተደረገላቸው በኋላ የጥራት ማረጋገጫ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ የምርት ተደራሽነትን ለማስፋት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

የሃመን የምክር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ መንግስቱ ብርሃኑ፤ ድርጅቱ ለአንድ አመት ያክል ለተለያዩ ድርጅቶች በጥራት መስፈርት ዙሪያ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉና ማረጋገጫ ያልተሰጣቸው ድርጅቶች የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ በማሟላት ዓለም አቀፍ ገበያውን እንዲቀላቀሉ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም በኩባንያው ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ሙያተኞች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችን የጥራት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ83 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

በፓርኮቹ ከሚሰሩ ኩባንያዎች እስካሁን ባለው ሂደት 874 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማስገባት መቻሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም