ምክር ቤቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር የነበሩ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወሰነ

116

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር የነበሩ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በጋራ ክልል ለመመስረት ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

በጋራ ክልል ለመመስረት የጠየቁት ጌዴኦ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እና ቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶና አሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው።

በምክር ቤቱ የማንነት፣ አስተዳደርና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ ሥር የሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ያቀረቡት ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ መሆኑን ተመልክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄው ጤናማ የፌዴራል ሥርዓት በመፍጠር የሕዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር በአግባቡ መመርመሩም ተገልጿል።

በተጨማሪም በጋራ መደራጀቱ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በቋሚ ኮሚቴው ታይቷል።

በዚሁ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዞኖቹና ልዩ ወረዳዎቹ በጋራ ክልል መመስረት እንዲችሉ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቆታል።

በመሆኑም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ምክር ቤቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውክልና ሰጥቷል።

ቀሪዎቹ የሀድያ ዞን፣ ሀላባ ዞን፣ ከንባታ ጠንባሮ ዞን፣ ጉራጌ ዞን፣ ስልጤ ዞን  እና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ ክልል ይቀጥላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም