ደንና ተያያዥ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለመቀየር ይሰራል-ሚኒስቴሩ

78

ቦንጋ፣ ነሀሴ 12/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ደንና ተያያዥ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለመቀየር እንደሚሰራ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን በመገኘት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ  አከናውነዋል።

በክልሉ ካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ሚቺት ቀበሌ በተካሄደ ችግኝ ተከላ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዎችና  ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በወቅቱ እንዳሉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተጠብቆ የቆየው ደን ዛሬ ያለው ገጽታ ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ምሳሌ የሚሆን ነው።

"ሰፊና እምቅ የሆነውን የአካባቢው ደንና በውስጡ የሚለሙ እንደ ቅመማ ቅመሞችና ማር የመሳሰሉ ተያያዥ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለመቀየር ሚኒስቴሩ ከክልሉ ጋር በመተባበር በጥናት የተደገፈ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ደን እየጠበቀ ከደን የሚያገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማሳደግ እንደሚገባ  አመላክተዋል።

"ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት አቅም በመለየት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያስገኝ እንሰራለን" ያሉት ማኒስትር ዴኤታው በዛሬው እለት በክልሉ የተከናወነው ችግኝ ተከላ ነባራዊ ሁኔታን ለመቃኘት አላማ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የደን ችግኝ ተከላ ከዘመቻ ባለፈ ባህል መደረግ አለበት" ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም የነበረው ሥርዓት የተፈጥሮ ሀብታችንን እንድንጠቀም ምቹ ሁኔታ የፈጠረ አልነበረም" ብለዋል።

"የለውጡ መንግስት እስከታች ውስዶ በመደገፍ አርሶ አደሩ ጠብቆ ካቆየው የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት እያደረገ ነው " ሲሉ አክለዋል።

ክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከ229 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸውን ችግኞች ለመትከል አቅዶ 98 በመቶ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

በደን ውስጥ ከሚለሙ ምርቶች መካከል ቅመማ ቅመም አንዱ መሆኑን ጠቁመው በክልሉ በየዓመቱ ከ121 ሺህ ኩንታል በላይ  የቅመማ ቅመም ምርት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዘርፉን የገበያ ትስስር  በማስተካከል  የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ በሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም