የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘበት ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

155

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 11/2014(ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የ”ኢትዮጵያ ታምርት” የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ አስታወቁ።

በተያዘው የበጀት ዓመተ ከዘርፉ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ይፋ የተደረገው የ”ኢትዮጵያ ታምርት “ ሀገራዊ የኢንዱስትሪ  ንቅናቄ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡

ለዓመታት ተቀናጅቶ ባለመስራት ተዘግተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች መልሰው ማምረት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ በማስገባት ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረና የኢንዱስትሪዎች የመወዳደር አቅም እየጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው አቶ ታረቀኝ ገለፃ፤ የሀገሪቱ ዓመታዊ ምርት ከ108 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፤ አብዛኛውን የመሪነት ድርሻ የሚወስደው ግብርና ነው፡፡

ሆኖም  በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የኢንዱስትሪ ፣ የኮንስትራክሽንና የማዕድን ዘርፎች የመሪነት ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመው፤ የአምራች ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ድርሻ አሁን ካለበት የ6 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ግብ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡

ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚያድግና 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ በኢንዱስትሪው ዕድገት 13 ሺህ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ እንደሚገቡ አስረድተዋል፡፡

በበተያዘው የበጀት ዓመት ብቻ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለ365 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤  ድሬዳዋ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ መናኸሪያና ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠና ለማድረግ በቅንጅት  እየተሰራ ይገኛል፡፡

በድሬዳዋ እየተዘረጉ ያሉ የኢንዱስትሪ መሠረተ-ልማቶች ለዘርፉና ለሀገር አቀፉ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የሰጠው ትኩረትና እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች የታሰበው ለማሳካት እንደሚያግዙ አብራርተዋል፡፡

ከተጀመረ የተወሰኑ  ወራትን ያስቆጠረው  የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ስራ እየገቡ፤ ባለድርሻ አካላትም ተቀራርበው መስራት የጀመሩ ሲሆን፤ ንቅናቄው  የሀገር ውስጥ ችግሮችና ዓለማቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከመፍጠር እንደሚዘልቅ  ተመልክቷል።

ንቅናቄው በ2022 ዓ.ም እንደ ሀገር የበፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ሰፊ እድል እንደሚኖረው ቀደም ብሎ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም