በአዲስ ዕይታ የተነቃቃው የግብርና ዘርፍ

392

ኢትዮጵያ ለግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ምቹ ስለመሆኗ ለዘመናት ሲነገር የቆየ እውነት ነው። ነገር ግን ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል አድጎ አገራዊ ፍጆታን ሸፍኖና ለወጪ ንግድ በሚገባ ቀርቦ የውጭ ምንዛሪ ለመሸፈን አልቻለም። ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫና በአገራዊ ራዕይ የተቃኘ ቁርጠኛ አመራር ያለመኖር ተጠቃሽ ነው።         

ኢትዮጵያን በአዲስ የልማት እና የዕድገት ሀዲድ ላይ ለማሳፈር በቅድሚያ በአዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ የተቃኘ፤ ቁርጠኝነትንና አገራዊ ርዕይን የሰነቀ ፖለቲካዊ አመራር የመፍጠር ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም። ከአራት ዓመታት በፊት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ አመራር ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል አመራር ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። የፖለቲካዊ አመራሩን በአዲስ ዕይታ አስተሳሰቡ ብቻ ሳይሆን አሰራሩንም በዚህ መልኩ እንዲቃኝ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት “አጓጊ ውጤቶች” ተመዝግበዋል።

ቀደም ሲል በግብርናው ዘርፍ  ትኩረት ተነፍጓቸው ለቆዩ አካባቢዎች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት፣ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት፣ በኢንዱስትሪው፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ በመንገድና በግንኙነት መሰረተ-ልማት ዝርጋታ፣ በተቋማት ሪፎርም፣ በወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለመፍጠር እና ለማጠናከር እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን ከድባቴው ለማላቀቅ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የተሰሩ እና እየተሰሩ ባሉ ስራዎች አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን በቅርቡ በተከናወነ መንግስታዊ የግምገማ መድረክ ላይ ተመልክቷል። 

የኢኮኖሚው ራስ-ግብርና

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽ የግብርናው ዘርፍ መሆኑን የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ግብርናው የአገር ኢኮኖሚ ራስ ሆኖ እዲዘልቅ ምርታማነትን በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አስተሳሰብ በተቃኘ አመራር እና ባለሙያ መደገፍ እንደሚገባ በዘርፉ ላይ ምርምር ያደረጉ አካላት ምክረ-ሃሳቦችን ያቀርባሉ፡፡

በዚህ በኩል አዲሱ አመራር በሁሉም ዘርፍ ውጤት ለማምጣት አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ዕይታ (ኒው ፓራዳይም) እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ያሳወቃል። የፖለቲካ አመራሩ በአዲስ አስተሳሰብ እና በአዲስ አተያይ ከተቃኘ እንዲሁም አገራዊ ርዕይን በዋና የልማት ስንቅነት ከያዘ ማሳካት የማይቻል ህልም እንደሌለ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች አመራር አባላት በግብርና ዘርፉ ላይ ያከናወኑት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የአገርን ኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጠ እንደሚቻል አመላካች ሁኔታዎቸ አሉ። ይህን እውነታ ወደ ውጤት ለመቀየር ደግሞ ከፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት፣ አዲስ አስተሳሰብ እና ዕይታ ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ያለውን የእንስሳ እምቅ ሀብት ወደ ውጤት ለመቀየር በእርባታ፣ በመኖ ልማት፣ በጤና እንክብካቤ እና መሰል ድጋፍ ለማድረግ በሳይንሳዊ መንገድ የታገዘ ስራ እየተሰራ እንዳለው ሁሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ምርምሮችን ማጠናከር ተገቢ ነው። እንዲሁም እምቅ አቅም ያላቸውን ሌሎች አካባቢዎችን በማሰስ አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠይቃል፡፡    

ያልታረሰው ለም መሬት

ለግብርና ምቹ እና ድንግል የእርሻ መሬት ያላቸው የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ከእንስሳት እርባታ ተግባር በተጨማሪ በእርሻ ስራ እንዲሰማሩ የማድረግ እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ ነው። የቆላማ አካባቢዎች ወቅታዊ የግብርና እንቅስቃሴን ላስተዋለ ወትሮም የፖለቲካ አተያይ ሲቃና አገር እንደምትስተካከል ጥሩ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ የለውጥ አመራሩ ለግብርና ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ከቴክኖሊጂ በስተቀር መሬቱም፣ አየሩም፣ ውሃውም፣ አምራች ሀይሉም እንዳላቸው ቀደም ሲል ቢታወቅም ትኩረት በመነፈጋቸው ብቻ እነዚህ ሁለት ክልሎች በሄክታር ከ40 እስከ 45 ኩንታል ስንዴ ምርት የመስጠት አቅም አላቸው።

በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የእርሻ መሬቶች ለምነታቸው እንዳለ ነው። በአካባቢው የነበረው አርብቶ ብቻ የማደር ሁኔታ ወደከፊል አርሶ አደርነት እየተቀየረ መምጣቱ ብዙ ካልታረሰው ማሳ ብዙ ምርት ለመሰብሰብ ያስችላል። ወደ ዘርፉ የሚገቡትንም ነዋሪዎች በሚጨበጥ ተስፋ በስራቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ጉልበት ይሆናል።

ኢትዮጵያ “አሉኝ” ከምትላቸው የኢኮኖሚ ምንጮች መካከል ከፍተኛ ምርት ለማምረት፣ የተሻሻለ እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብና የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ አቅም ያለው፣ ከፍተኛ የስራ ዕድል የሚፈጥር፣ ከኢትዮጵያውያን የዕለት ተለት የህይወት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የኢኮኖሚው ራስ ግብርና ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከምትታወቅባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱና ዋናው ግብርና ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ከግብርናው ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ካልቻለችባቸው ምክንያቶች መካከል የአመራሩ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማነስ፣ ለግብርና ልማት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቶ አለማወቅ፣ የግብርና ቴክኖሎጂ ልምምድ አለመኖር፣ የግብርና ባለሙያዎች ተደራሽነት አናሳ መሆን በዋናነት የሚጠቀሱ እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡

የለውጥ አመራሩ ይዞት ብቅ ባለው አዲስ አስተሳሰብ እና አተያይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከፍተኛ የዕይታም ሆነ የአሰራር እንዲሁም የምርት ለውጥ እና ዕድገት እያሳዩ ካሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ አሁንም የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአርሶ አደሮችንና የአርብቶ አደሮችን ውጤታነት ማየት ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እና ለምርት ማደግ፣ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ማደግ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከግብርናው ባሻገር በሌሎች ዘርፎችም እንድንሰማራ አቅም ፈጥሮልናል ሲሉም በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ይናገራሉ፡፡

እንደመውጫ

በከፍተኛ አመራሩ ላይ የተፈጠረው ጅምር አዲስ አተያይ እና ዕይታ ምክንያት በግብርና ዘርፉ ላይ የተመዘገበውን ውጤት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ማስፋት እና የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አስተሳሰብን እና ዕይታን (ኒው ፓራዳይም) የሚለውን እሳቤ ወይም ግንዛቤ እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ባሉ አመራር አባላት ዘንድ ማስረጽን ይጠይቃል፡፡   

“ብረት የሚቀጠቀጠው እንደጋለ ነው” የሚለውን ብሂል መነሻ በማድረግ በግብርናው ዘርፍ በተለይ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎችየተጀመረው አዲስ አተያይ እና ከግብርናው ዘርፍ የተገኘው ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአርሶ እና አርብቶ አደር ህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚሰራውን ስራ በግልጽ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተገኘውን መልካም ልምድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋትንም ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር እና የክልል ግብርና ቢሮዎችም ሆኑ በግብርናው ዘርፍ የምርምር ስራ የሚሰሩ ተቋማት በአገሪቷ ውስጥ ከሚገኙ የግብርና ተመራማሪዎች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በጋራ መስራት የተጀመረው የአዲስ አስተሳሰብ እና አዲስ ዕይታ እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም