ህገ ወጥ የማዕድናት ልማትና ዝውውርን ለመግታት መረባረብ እንደሚገባ ተጠቆመ

95
አዳማ ግንቦት 11/2010 በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ህገ ወጥ የማዕድናት ልማትና ዝውውርን ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረብ እንደሚገባ የማዕድን ፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አሳሰቡ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልል የማዕድን ቢሮዎችና የዘርፍ ተጠሪ ተቋማት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ እየመከረ ነው። በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕድን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዓለሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ህገ ወጥ የማዕድናት ልማትና ዝውውር በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል። በያዝነው የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላኩ የማዕድናት ምርት 600 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ እስካሁን የተገኘው ገቢ 118 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ለዕቅዱ አለመሳካት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ህገ ወጥ የማዕድናት ልማትና ዝውውር መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ይህም ከውጭ ምንዛሬ አንጻር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በእጅጉ እንዳሳነሰው ገልጸው ችግሩን ፈጥኖ ለመቀልበስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብና የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። "የማዕድናት ምርቶች ሀገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍና የኢንዱስትሪ ግብዓት በማቅረብ በኩል ሚናው የጎላ ስለሆነ በዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ሚኒስቴሩ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል። መድረኩ የተዘጋጀው ዘርፉ ያለበትን ውስብስብ ችግሮች በመለየትና በመፍትሄ ሀሳቦች ላይ በመግባባት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አብራርተዋል። ይህም ከክልሎች ጋር ያለውን የቅንጅት ሥራ ለማጠናከርና የማስፈጸም አቅምን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት። በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ነጋሳ በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት የዘርፉን ልማት ለማፋጠን የሚያስችል ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን የማስገኘትና የማዳን እንዲሁም የሥራ ዕድልን የማሳደግ ሥራዎች ላይ አተኩሮ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን  አመልክተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በነዚህ ዙሪያ ከተከናወኑት ሥራዎች 22 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የኢንቬስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ 18 ኩባንያዎች የማዕድን ልማት ፈቃድ ወስደው ወደሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቅሰዋል። ከእዚህ በተጨማሪ 2 ሺህ 395 ኪሎ ግራም ወርቅና 71 ሺህ 732 ሜትር ኩብ ዕምነበረድ ተመርቶ ጥቅም ላይ መዋሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከልዩ ልዩ የማዕድን ሥራዎች 120 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አቶ ገረመው ተናግረዋል። የባዮኢታኖልና የባዮዲዝል ተክሎችን ልማት በማስተባበር ምርቱ እንዲቀርብ የማድረግ፣ የካርቦን ልቀትን መቀነስና ባዮፊውል ለተለያየ አገልግሎት እንዲውልና በነዳጅ ተቋማት የመቀየጫ ፋሲሊቲዎች እንዲገነቡም ጥረት መደረጉን አስረድተዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የማዕድን ቢሮዎችና የዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም