በመዲናዋ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ወጤታማ የሙከራ ትግበራ ተከናውኗል –የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

134

ነሃሴ 10/2014/ኢዜአ/ በ2014 የትምህርት ዘመን በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ የተካሄደው የሙከራ ትግበራ ውጤታማ እንደነበር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከግልና ከመንግስት የትምህርት ተቋማት ጋር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ በ44 ትምህርት ቤቶች ላይ መካሄዱን ገልጸዋል።

በዚህም በሙከራው የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት በ2015 የትምህርት ዘመን አዲሱን ስርአተ ትምህርት ለመተግበር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡    

አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ፣የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ የትምህርት ተቋማትና መምህራን በሙሉ አቅማቸው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለትግበራው ስኬታማነት ሁሉም ተቋማት ወጥነት ያለው የትምህርት አሰጣጥ እንዲከተሉ ትምህርት ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራም አቶ አድማሱ አመልክተዋል።

የማስተማሪያ መጽሃፍትና የመምህራን መመሪያዎች ተዘጋጅተው በሕትመት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ፣ የ8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ እና የ12ኛ ክፍል የማጠናቀቂያ ፈተና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የሚሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ በበኩላቸው ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ሰፊ ክፍተቶች እንደነበሩበት አስታውሰዋል።

በተለይ በግል የትምህርት ተቋማት ያለው የትምህርት አሰጣጥ ወጥ ባለመሆኑ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የትምህርት ጥራትን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ማረጋገጥ እንደሚቻል አመልክተዋል።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አገር በቀልና ዓለም አቀፋዊ እውቀትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የትምህርት አሰጣጡ ወጥ እንዲሆን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በተለይም የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በሥርዓተ ትምህርቱ ትግበራ ላይ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም መስል መድረኮች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ የትምህርት ተቋማት ባለቤቶች፣ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።