ከልዩነቶቻችን ይልቅ ለአንድነታችን፤ካለፈው ይልቅ ለአሁኑ አጽንኦት መስጠት አለብን-ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

112

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)''ከልዩነታችን ይልቅ ለአንድነታችን፤ ካለፈው ይልቅ ለአሁኑ አጽንኦት መስጠት ይጠበቅብናል'' ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናግሩ።

በኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበርና በፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን ትብብር የተዘጋጀ አውደጥናት "ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ፣የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ፣የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምሁራን ተገኝተዋል።

የማህበሩ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ረጅምና ደማቅ ታሪክ ያላት አገር ነች ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ የፖለቲካ ግብግብ አውድማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና አለመግባባቶች እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመው በ1983 የተደረገው የስርአት ለውጥ መፈክሩ "ህብረ ብሔራዊ አንድነት" ወይም "አንድነት በብዝሀነት" ቢሆንም አንድነቱ ሳይሆን ብዝሀነቱ ገኖ ወጥቷል ብለዋል።

የታሪክ ሰነዶች እና ማስረጃዎች የሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እና ክልሎች ምንም እንኳን የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ ባህርያት እና ተቋማት ቢኖራቸውም በብዙ መንገድ እርስ በእርስ የተሳሰሩና የተጋመዱ ናቸው ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

ህብረ ብሔራዊ ትስስር የተሞላው የታሪክ ሀቅ በተለይም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ጎልቶ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ማህበሩ ከተቋቋመበት አላማዎች አንዱ ታሪክና የታሪክ ትምህርት ለብሔራዊ መግባባት ስለሚውልበት ሁኔታ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲሆን የዛሬው መድረክም ለብሄራዊ መግባባት የድርሻውን ለማበርከት ያለመ ነው ብለዋል።

ማህበሩ በቀጣይ መሰል መድረኮችን እንደሚያካሂድ ገልጸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ለማህበሩ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም